22/10/2023
ለምን ህይወታችንን በበዛ ግዴታ እንጨምቀዋለን?
በምርጫችን አልመጣንም፤ በምርጫችንም አንሔድም።
ህይወት ያለው ሁሉ በመኖር ትግል ውስጥ ማለፉ ጤናማና የሚጠበቅ የተፈጥሮ ሒደት ነው። በዚህ መነሻ ካየነው ራስን ማጥፍት ፀረ- ተፈጥሮ ተግባር ይሆናል።
ተፈጥሮ ያዘጋጀችን ያለንን አቅም ተጠቅመን ለመኖር ነው ብለን ከተነሳን ራስን ማጥፋት የተፈጥሮን ፍሰት ማቋረጥ፣ ጉዞዋን ማኮላሸት ነው። ይህ ማለት ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች ተወቃሽ ናቸው ማለቴ አይደለም። አልችል ብለው እንጂ ሲሆንማ መኖር ማን ይጠላል?
አብዛኛዎቻችን የግድ ይህ መሆን አለበት፣ የግድ ይህን ማሳካት አለብኝ፣ ደስተኛ ለመሆን የግድ ይህ መሟላት አለበት የሚሉና መሰል የፍፅምና አስተሳሰቦች ደስታችንን ያደፈርሱታል። ገዢ አስተሳሰቦች ሲሆኑም ወደ ከፋ ቀውስ ሊገፉን ይችላሉ።
ራስን ማጥፋት የደሀ እጣ የሚመስላቸው ሰዎች አሉ። እውነታው ራስን ማጥፋት ከቁስ ድህነት ይልቅ ከተስፋ ድህነት ጋር በቀጥታ ይያያዛል።የምንኖርበት ቁስ ማግኜት አስፈላጊ ጉዳይ ቢሆንም ትርጉም ያለው ህይወት ለመኖር ዋስትና አይደለም። መኖሪያችንን ሰርተንም ሰርቀንም ልናሳካው እንችል ይሆናል።የምንኖርለትን ምክንያት ፈልገን ማግኜት ሌሎች የሚሰጡን ፣ እንደ ሀብት ቤተሰብ የሚያወርሰን ወይም ከሰማይ የሚወርድልን መና አይደለም። ይልቁንም ከህይወት ውጣ ውረድ ፈልቅቀን የምናወጣው የምርጫችን ውጤት እንጂ።
በናዚዎች ጭካኔ እንደ እኤአ ከ1942-1945 ባሉት አመታት በተለያዩ የማጎሪያ ጣቢያዎች የከፋ ስቃይን ያሳለፈው ቪክቶር ፍራንክል (ዶር) በእያንዳንዱ ህይወታችን ውስጥ ምርጫ እና አንፃራዊ ነፃነት አለን ብሎ ያምናል። በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ሳይቀር አጋቾች ሊቆጣጠሩት የማይቻላቸው መንፈሳዊ ነፃነት አለን ይለናል።
መከራ እና አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ የህይወትን ትርጉም ፈልቅቀን የምንወጣበትን የተፈተነ ልምድ Man's search for meaning በሚል መፅሐፍ ከተቦልን አልፏል።የExistentialism አቀንቃኞች በአግባቡ የሚኖር ህይወት ስለሞት ካለ ጥልቅ መረዳት ይመነጫል ይሉናል። የመኖር ዋናው ምክንያት ደግሞ ከስቃያችን ፈልቅቀን የምንቀዳጀው የህይወት ትርጉም ነው። የህይወት ትርጉሙ ሲጠፋብን የኦናነት ስሜት (Sense of vacuum) ይፈጠራል። በጊዜ ካልተፈታ በተራው ወደራስን ማጥፋት ይመራናል የሚል እይታ አላቸው።
#ስለ ራስን ማጥፋት አንዳንድ ነገሮች
ራስን ማጥፋት ድንገቴ ጉዳይ አይደለም። ብዙ ጊዜ ታስቦበት የሚፈፀም እንጅ። አብዛኞቹ የዚህ ችግር ሰላባዎች የታወቀም ይሁን ባልታወቀ የስነልቦና ህመም የሚሰቃዩ ናቸው። ራሳቸውን ከሚያጠፉት ይልቅ ራስን በማጥፋት ስሜት የሚሰቃዩት በበዙ እጥፍ ይበልጣሉ። ስለሆነም የዚህ ስሜት ተጠቂዎች ሌሎች እንዲረዱላቸው እና እንዲያውቁላቸው ተደጋጋሚ ጥረቶች ያደርጋሉ።
ራስን ማጥፋት ለመኖር አቅም የማጣት ውጤት ነው። ይህ ስሜት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠነከረ የሚመጣ ሲሆን የተግባር ምልክቶችም አሉት።
1. ተደጋጋሚ ስለራስ አሉታዊ ንግግር (Negative self talk)
እኔ ለማንም አልጠቅምም፣ አልረባም፣ ዋጋ የለኝም፣ የቤተሰብ ሸክም ነኝ እና መሠል ሀሳቦች
2. ራስን መበዝበዝ (Self distractive behavior)
ራስን በሚጎዱ ድርጊቶች መዘፈቅ፣ ለህይወት የበዛ ደንታ ቢስነት፣ በአልኮል-እፅ መዘፈቅ፣ በተደጋጋሚ ጥንቃቄ የጎደለው የግብረስጋ ግንኙነት መሳተፍ፣ ምክንያት አልባ አደጋዎችን መጋፈጥ
3. ረዘም ላለ ጊዜ በአሉታዊ ስሜቶች መሰቃየት -ከፍተኛ ፀፀት፣ ድባቴ፣ ሀዘን፣ ትርጉም አልባነት፣ የመነጠል ስሜት ወዘተ
ተጠቂዎች እነዚህን ካለፉ በኋላ ወደ መጨረሻ ደረጃ ሲደርሱ ስለሞት በተደጋጋሚ ማውራት፣ ከህይወት እረፍት እንደሚፈልጉ መለፈፍ፣ ራስን የማጥፊያ አማራጮችን ማማተር እና የስንብት/ኑዛዜ መልዕክቶች መተው የተለመዱ ናቸው።
# ምን አይነት እገዛ ይፈልጋሉ?
እመለስበታለሁ