11/11/2024
ጤና ምንድን ነው፤ ጤናማነት ሲባልስ ምን ለማለት ነው?
🌍የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ከ1948 ዓ/ም ጀምሮ ጤና ማለት "የሥነ አካል፣ የአእምሮ እና ሥነ ማኅበራዊ ኹነቶች ፍጹማዊ ደህንነትን በምልአት እንጂ የበሽታዎች አሊያም የአካላዊ ጎደሎነት አለመኖር ብቻ አይደለም።/A state of complete physical, mental, and social well-being and not merely the absence of disease or infirmity." በማለት የትርጉም ብያኔ ያስቀመጠለት ሲኾን ይኽም በዓለም ጤና ድርጅት መተዳደሪያ የጋራ ቃልኪዳን ሰነድ (Constitution of World Health Organization) ላይ ሰፍሮ ይገኛል።
👨⚕️ጤናማ ሕይወት (Components of healthy life) ለመከወን የሚረዱንን ነገሮች ደግሞ እስኪ በመጠኑም ቢኾን አብረን እንይ፦
ሀ. ሥነ አካላዊ ጤና (Physical Health)፦ ነፍስ ያለ አካለ ስጋ በግዘፍ ቀዋሚ እንዳላይደለች ኹሉ ለመኖራችን ዋናው አካላዊ ጤናችን ነውና እነሆ፦
፩. 🏃♂️ መደበኛ አካላዊ ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ (Regular exercise)፦ የልብና ደም ሥር የጤናማነት ሥርዓትን ያስተካክላል፤የጡንቻ ጥንካሬንና ብርታት፤ ተጣጣፊነትን እንዲሁም ጭንቅ ቻይነትን ያጎናጽፋል።
፪. 🧑🍳 የተመጣጠነ አመጋገብ (Balanced Nutrition)፦ በአትክልትና ፍራፍሬ፤ በእህል ዘሮች የተቀመመ ከቅባትና ከስብ መጠኑ ሳይበዛ በልኩ የተቀመመ ጤናማ/ሜዲትራኒያኒዊ ምግብ አይነት (Mediterranean diet) የሚባለውን ማዘውተር ወሳኝነት አለው።
፫. 🛌 በቂ እንቅልፍ (Adequate sleep):- እንደየዕድሜያችንን ክልል የሚለያይ ቢኾንም ለአዋቂዎች በቀን ውስጥ በአማካይ 7-9 ሰዓታትን የእንቅልፍ እረፍትን ማግኘት እጅግ በጣም ከፍ ያለ ረብ አለው።
፬. የመከላከል የጤና እርምጃዎች (Preventive Health Care)፦ ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ ይበጃል እንዲሉ መደበኛ የኾኑ የጠቅላላ ጤና ምርመራ (Regular Medical checkups) ማድረግ፣ ክትባቶችን እንደየአስፈላጊነቱ መከተብ፣ የጤና ማጣሪያ ክትትሎችን (health screenings) ከዘርፉ ሐኪሞች ጋር በመመካር ማሰራት እና የመከላከል እርምጃዎችን መውሰድ አካላዊ ጤናችን ለመጠበቅ በአያሌው ይረዱናል።
ለ. የሥነ አእምሮ ጤና (Mental Health)፦ ያለ አ እምሮ ጤና ጤና የለምና ለሥነ አእምሯችንን ደህንነትም እንዲሁ ግድ ሊለን ይገባል፦
፩. የስሜት ደህንነትን ማስጠበቅና የአዎንታዊነት ሥነ ልቦናን አስችሎ ማጽናት (Emotional wellbeing) ፦ ይኸውም አሌ የማይባል ድረሻ አለውና ደግ ደጉን በማሰብ ክፋትና ተንኮለኛነትን፤ ሸርና ደባን፣ ምቀኝነትና አልጠግባይ ስሱነትን ማስወገድ እነሆ ክቡር ከበደ ሚካኤል "ጽድቅና ኩነኔ ቢኖርም ባይኖርም፤ ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም።" እንዳሉት አዎንታዊ ሰው መኾን አብዝቶ ከፍ ያለ ጠቀሜታ ያስገኛል።
፪. ጭንቀትን ሀይ ማለት (Stress Management)፦ አስቦ መኖር አግባብ እና ተፈጥሯዊ ቢኾንም መጨነቅ ግን አላስፈላጊና ጎጅ በመኾኑ ይኽንኑ ሊያቀሉ የሚችሉ እንደመጸለይ እና ማመስገን ፤ በመመሰጥ ወደ በመተንፈስ ራስ ማዳመጥና ጊዜ መስጠት ከንዴት ይልቅ በእርጋታ መለማመድ ሊያጣጥሉት የማይገባ ጉልህ ድርሻ አለው።
፫. አዋቂዎችን ማማከር (Seeking mental health support)፦ የስሜት መረበሽ፣ የድባቴ አሊያም የጭንቀት ስሜት ቢገጥም ባለሙያዎችን ለማማከር ቸል መባል አይገባውም።
ሐ. የሥነ ማኅበራዊ ጤና (Social Health)፦ ለሰው ሰው ነው ልብሱ እንዲሉ አባቶቻችን የአንዳችን መኖር ለሌላኛችን ተስፋ ነውና በጋርዮሽ መኖራችን ደግሞ ጤናማነት እንዲኖረው፦
፩. በአለኝታነት እንጂ በጥቅም ቁርኝት ያልተመሰረተ ግንኙነትን በእውነት መመሥረትና ይህንኑ አጽንኦት ሰጥቶ እየተደጋገፉ መጽናት
፪. የማኅበረሰብ ደራሽነትና የበጎነት ተግባራት ላይ የፈቃደኝነት ስኬታማ ተሳታፊነትን ማጎልበት ጭምር ለጤናማነት አስተዋጽኦ ያደርጋል።
፫. የማኅበራዊ መረዳጃ ባህላዊ ተቋማት ለምሳሌም እንደ ዕድር እና ዕቁብ ባሉ በችግር ጊዜ ደራሽ አካላት ጋር የግንኙነት ተሳትፎን ማጎልበትም ይመከራል።
እነሆ ጤናማ ለመኾን ከላይ ያልናቸው ኹሉ በተናጠል ያይደለ በአንድነት ተገምደው ያስፈልጉናል እና ኹልጊዜም በምልዓት ትኩረት ለጤናችን!