
19/05/2025
ከኢትዮጵያ ሕክምና ማህበር የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
ግንቦት 10 ቀን 2017ዓ.ም አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ
የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር በአገሪቱ ሃኪሞች እንዲሁም የጤና ባለሙያዎች የሚነሱ ጥያቄዎችን አስመልክቶ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት የተለያዩ የሙያ ማህበራትን እና ስፔሻሊቲ ሶሳይቲዎችን በማስተባበር ዉይይት በማድረግ እንዲሁም ሙያ ማህበራቱ ከጤና ሚኒስቴር ጋር ተከታታይ ውይይቶች እንዲያደረጉ በማመቻቸት ጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠዉ እና አስቸኳይ መፍትሄ እንዲቀመጥ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ ቀይቷል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በአሁን ሰዓት በተወሰኑ የጤና ተቋማት የጤና አገልግሎት እና ትምህርት እየተስተጓጎለ መሆኑን ሰምተናል፡፡ ይህንንም አስመልክቶ ማህበራችን በሚከተሉት ጉዳዮች ላይ የሚመለከተዉ አካል ትኩረት እንዲሰጥበት ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
1. ሃኪሞቻችን በሚያነስዋቸው ጥያቄዎች ማለትም የደመወዝ ማነስ፣ የጥቅማጥቅም፣ የስራ ቦታ ደህንነት እንደ ኢትዮጵያ ሕክምና ማህበር ተገቢ መሆኑን የምንቀበል እና ለረጅም ጊዜያት ለሚመለከተው ባለድርሻ አካል ጉዳዩን ስናቀርብና ስንሰራበት ቆይተናል፡፡ ሆኖም በአሁኑ ሰዓት የጉዳዩ አሳሳቢነት እየጨመረ በመምጣቱ የሚመለከተው አካል አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጥበት በዚህ አጋጣሚ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
2. አሁን ያለዉ ሁኔታ ማለትም የጤና አገልግሎቱ እና የትምህርት ሂደቱ በምንም አይነት ደረጃ ቢሆን መስተጓጎሉ ማህበረሰቡን፤የጤና ባለሞያዉን እንዲሁም የጤና ስርአቱን እጅግ ሊጎዳ የሚችል በመሆኑ ማህበሩ ይህ ጉዳይ ወደተባባሰ ደረጃ ከመድረሱ በፊት የጤና ሚኒስቴርና የሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ከባለሙያዎች ጋር በመሆን አፋጣኝ የሆነ ሃገራዊ ዉይይት በየደረጃዉ እንዲያካሂዱ እና ችግሮቹ በዉይይት እንዲፈቱ እንዲደረግ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
3. ሃኪሞቻችን እንዲሁም የጤና ባለሙያዎች አሁን ካለው ሁኔታ ጋር ተያይዞ በተለያዩ ቦታዎች ለእስር እንደተዳረጉ ሰምተናል፡፡ በመሆኑም ባለሞያዎቹ ከእስር እንዲፈቱ እና ወደስራ ገበታቸዉ ተመልሰዉ ለማህበረሰቡ አገልግሎቱን እንዲሰጡ ቢደረግ የተሻለ እንደሆነ እና በዚህ ረገድ የሚመለከታቸዉ አካላት አስፈላጊዉን እገዛ እንዲያደርጉ እናሳስባለን፡፡
4. ማህበራችን እንደወትሮው ችግሮችን ለመፍታት እና መፍትሄ ለመስጠት ከጤና ሚኒስቴርም ሆነ ባለድርሻ አካላት በሚያደርጓቸዉ ጥረቶች ላይ ከዚህ ቀደም ሲያደርገዉ እንደነበረዉ ሁሉ አብሮ ለመስራት እና ትብብሩን አጠናክሮ በመቀጠል የመፍትሄዉ አካል ለመሆን ዝግጁ እንደሆነ ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡