20/06/2024
የመጨረሻው ክፍሎች አንድ ላይ!
ምዕራፍ 12
ለቅሶ አድክሟት ነበር የተኛችዉ፡፡ በማግሰቱ ጠዋት ከመኝታዋ የሚያስነሳ ስራም ሞራልም ስላልነበራት እስከምሳ ሰዐት ከአልጋዋ አልወጣችም፡፡ እንቅልፍ ባይወስዳትም ተነስታ መብላት ወይ ከእናቷ ጋር ማወራት አላሰኛትም፡፡ ከአልጋዋ አዘልሎ ያስነሳት አንድ የስልክ ጥሪ ነበር፡፡ ቁጥሩን ስለማታዉቀዉ ምናልባት መስፍን ከሆነ በሚል ነቃ ብላና ጉሮሮዋን አፀዳድታ ‹‹ሄሎ›› አለች፡፡ ‹‹ቤቴልሄም?›› የሚል የሴት ድምፅ ስትሰማ ግን ሀሞቷ ፈሰሰ፡፡ የደወለችዉ ሴት ከአንድ መስሪያቤት መሆኑንና ለስራ ቅጥር እንደፈለገቻት ስትነግራት ግን ወዲያዉ ስሜቷ ተቀየረ፡፡ ሴትየዋ ዛሬዉኑ የትምህርት ማስረጃዎቿን ይዛ እንድትመጣ ከነገረቻት በኋላ የመስሪያቤቱን አድራሻ ነገረቻት፡፡
ስልኩን እንደዘጋች በፍጥነት ከአልጋዋ ወርዳ ራሷን ማዘጋጀት ጀመረች፡፡ መስፍን በዚህ ፍጥነት እንዴት ስራ እንዳገኘላት በመገረም ጊዜዋን ማባከን አልፈለገችም፡፡ ይህንን ሀሳብ ለበኋላ ልታቆየዉ ነዉ፡፡ ካሏት ልብሶች ዉስጥ ለቢሮ የሚመጥን ባይሆንም የተሸለ ያለችዉን መርጣ ለበሰች፡፡ ፀጉሯን አበጥራ አስያዘች፡፡ ዶክመንቶቿን መርጣ ከሰበሰበች በኋላ እየተጣደፈች ወጣች፡፡ በመንገዷ ስራዉ እንዲሳካላት ያለማቋረጥ እየፀለየች ነበር የተባለዉ ቦታ የደረሰችዉ፡፡ ቦታዉ ላይ ስትደርስ መስሪያ ቤቱ ያለበት ህንፃ ትልቅነትና ማማር በራሱ እያስፈራት ነበር የገባችዉ፡፡ ሰፊዉ የህንፃዉ የመጀመሪያ ክፍል ላይ ያገኘቻት ተቀባይም ሆነች ወዲያ ወዲህ የሚሉት ሌሎች ሰራተኞች የለበሱት አለባበስና አረማመድ ለቦታዉ እንደማትመጥን እንዲሰማት ቢያደርጋትም እንደምንም ራሷን በማበረታት ስራዉን ልታገኝ እንደምትችል ማመን ነበረባት፡፡ እንግዳ ተቀባይዋ ስሟንና የመጣችበትን ምክንያት ከጠየቀቻት በኋላ አስከትላት በሊፍት ወደ አስረኛ ፎቅ ይዛት ወጣች፡፡ ከሊፍቱ እንደወጡ ወደ አንድ ክፍል ይዛት ስትገባ ነበር የደወለችላትን ሴት ያገኘቻት፡፡ ሴትየዋ ወደዉስጥ ካለዉ የግል ያማረ ሰፊ ቢሮዋ ይዛት ከገባች በኋላ እንድትቀመጥ ጋበዘቻትና የትምህርት ማስረጃዎቿን መመርመር ጀመረች፡፡ ስትጨርስ አንዳንድ የተለመዱ ጥያቄዎች ብቻ ጠይቃት የስራ ቅጥር ዉል እንድትፈርም ወረቀት አቀረበችላት፡፡ ነገሩ በፍጥነትና ያለእንከን መከናወኑ ግራ እየገባት ዉሉን ማንበብ ጀመረች፡፡ በዉሉ ላይ የስራ መደቧ ረዳት ማናጀር እንደሆነ ተገልፃል፡፡ ከስራ መደቡ በላይ ያስደነገጣት ግን የደሞዙ ነበር፡፡ በፅዳት ሰራተኝነት ከምታገኘዉ ሁለት እጥፍ ነበር፡፡ ቀና ብላ ሴትየዋን አይታት ‹‹ግን…›› አለቻት የምትናገረዉ እየጠፋት፡፡ ‹‹ግን ለዚህ ስራ…ማለቴ ለዚህ ስራ መደብ… ትመጥናለች ብለሽ ታምኛለሽ?›› አለች፡፡ ሴትየዋ ፈገግ ብላ ‹‹በሚገባ! የተማርሽዉ ትምህርት ለስራዉ የሚመጥን ነዉ፡፡ ከተመረቅሽም ብዙም አልቆየሽም፡፡ ደግሞም ረዳት ማናጀር የተደረግሽዉ ለአድሚኒስትሬሽን (ለአስተዳዳር) ክፍሉ እንጂ ለጠቅላላ መስሪያ ቤቱ አይደለም፡፡ እኔ ማናጀር ነኝ፡፡ ስለዚህ ማወቅ ያለበብሽን ነገር አሳይሻለሁ፡፡ አንችን እንድቀጥር የጠቆመኝ ሰዉ ደግሞ ምንም እንኳ በዘርፉ ልምድ ባይኖርሽም ጠንካራ ሰራተኛ መሆንሽን ነግሮኛል››፡፡ መስፍን ሴትየዋን እንድትቀጥራት እንዳዘዛት ጥርጥር የለዉም፡፡ ምንም እንኳ እድሉን ያገኘችዉ በመስፍን ትዕዛዝ ቢሆንም የራሷን ብቃት በማሳየት ስራዉ በእርግጥም የሚገባት መሆኑን ማሳየት ትችላለች፡፡ ወረቀቱን ሳታመነታ ፈረመች፡፡ ሴትየዋ ስራዉን ለመጀመር የሁለት ቀን ጊዜ ሰጥታ አሰናበተቻት፡፡
ቤቲ በተሰጣት ሁለት ቀን ዉስጥ ለአዲሱ ስራ በቂ ዝግጅት አደረገች፡፡ ወ/ሮ ዉባለም በሰጠቻት ደሞዝ አንዳንድ የቢሮ ልብሶች ጫማና ቦርሳ ገዛች፡፡ ፀጉሯንም ከብዙ ጊዜ በኋላ ተሰራች፡፡ አሁን ለገንዘብ መጨነቅ የለባትም፡፡ ከአዲሱ ስራዋ የምታገኘዉ ገንዘብ ከበቂ በላይ ነበር፡፡ መስፍንን ልታመሰግነዉ ፈልጋ ነበር፡፡ ግን እሱ ካልፈለጋት እሷ ፈልጋ እንደማታገኘዉ ገብቷታል፡፡ የስራዋ ነገር በብዙ መልኩ ትኩረቷን ስለወሰደዉ ደስ ብሏታል፡፡ ቢያንስ አሁን በየደቂቃዉ ስለሱ ማሰቧን አቁማለች፡፡
ከሁለት ቀን በኋላ ስራ ስትገባ ከመጀመሪያዉ ቀን በተለየ የራስ መተማመኗ ጨምሮ ነበር፡፡ አሁን አለባበሷም የሚያሳፍር አልነበረም፡፡ አለቃዋም ቀናና መልካም ሴት ሆና አግኝታታለች፡፡ ከአንዲት ወጣት ረዳት ማናጀር ጋር የምትጋራዉ ያማረ ቢሮ ላይ ያረፈ ጠረጴዛና ወንበር ተሰጣት፡፡ ሁለቱም የሚሰሩት ለሴትየዋ ስለሆነ የስራዉን ዝርዝር ልጅቷ እንደምታስረዳት ተነግሯታል፡፡ ወጣቷ ረዳት ማናጀር ስሟ ሰላም እንደሚባል መስሪያቤቱ ዉስጥ ለ5 ወር እንደሰራችና ሌሎች ሌሎችንም ነገሮች ነገረቻት፡፡ ቀልቃላ ብትሆንም ተጨዋች መሆኗን ቤቲ ወዳላታለች፡፡ በእድሜም ብዙ ስለማይራራቁ በትንሽ ሰዐታት ዉስጥ እንደጓደኛ ማዉራት ጀምረዋል፡፡ ማናጀሯ ወ/ሮ አለምፀሀይ ምን አይነት ሰዉ እንደሆነች፤ ምን እንደምትወድና እና እንደምትጠላ፤ የሷ አለቃ የመስሪያ ቤቱ ምክትል ስራአስኪጅ እንደሆነ፤ ምን አይነት ሰዉ እንደሆነ… ቤቲ መስማት ከምትችለዉ በላይ ነበር የነገረቻት፡፡ ስለስራቸዉ እንደዚህ ዘርዝራ ብትነግራት ደስ ይላት ነበር፡፡ እንዳታስከፋት በማለት ግን ሁሉንም አዳመጠች፡፡
ቀኑ አልቆ ከስራ ሰወጡ ቤቲ ከመቼዉም በበለጠ ደስተኛ ሆና ነበር፡፡ ስራዉን ከመዉደዷም በላይ እንደተማረ ሰዉ ቢሮ መዋሏ ብቻ ለእሷ ትልቅ ነገር ነበር፡፡ በዛ ላይ ስለስራዉ ለማወቅና ለመማር ትኩረቷን ሰብስባ የነበረች ከመሆኗ በተጨማሪ ሰላም ቀኑን ሙሉ ፋታ ስላልሰጠቻት ስለመስፍን ለማሰብ ጊዜ አልነበራትም፡፡ በዚህ ከቀጠለች እሱን መርሳት ትችል ይሆናል፡፡ ስለሱ ስታሰብ የሚሰማት የጠለቀ ሀዘን የምትረሳበት መልካም አጋጣሚ ነበር፡፡ ቤት ገብታ ስለዉሎዋ ለእናቷ እየፈነደቀች ነበር የነገረቻት፡፡ እናቷም ልጇ ለፍታ ተምራ በመጨረሻ ዉጤቷን በማየቷ የደስታ ለቅሶ አለቀሰች፡፡
በማግስቱ በአዲሱ የደስታ መንፈሷ ነበር ስራ የጀመረችዉ፡፡ ረፋዱ ላይ ወ/ሮ አለምፀሀይ ለአንድ አነስተኛ የማናጀሮች ስብሰባ ወደስብሰባ አዳራሹ ስትሄድ ቤቲንና ሰላምን አስከትላ ነበር የሄደችዉ፡፡ ስብሰባዉ ላይ የሚነሱትን ሀሳቦች ሲፅፉ እስከምሳ ሰዐት ቆዩ፡፡ ሰላም ሰልችቷት የነበረ ቢሆንም ቤቲ ግን ስብሰባ ላይ ስትገኝ የመጀመሪያዋ በመሆኑ በደስታና በጉጉት ነበር የጨረሰችዉ፡፡ ከአዳራሹ ወጥተዉ ወደ ቢሯቸዉ በመመለስ ላይ ሳሉ ግን ድንገት ልቧን የሚተረክክ ሰዉ ኮሊደሩ ላይ አየች፡፡ መስፍን! ከአንድ ሰዉ ጋር በኮሊደሩ መጨረሻ ላይ ቆሞ ያወራል፡፡ ስታየዉ ከመደንገጧ የተነሳ እግሯ መራመድ አቆመ፡፡ ያስደነገጣት እሱ መሆኑ አልነበረም፡፡ አየዋለሁ ብላ ባልጠበቀችዉ ጊዜና ቦታ፤ እየረሳችዉ ሲመስላት ድንገት መከሰቱ ነበር፡፡ ሰላም ‹‹ነይ እንጂ›› አለቻት ወደኋላ ስትቀርባት፡፡ ‹‹እዚህ… እዚህ ምን ይሰራል?›› አለች ለራሷ በሚመስል ዝቅ ያለ ንግግር መስፍን ላይ እንዳፈጠጠች፡፡ ሰላም የቤቲን አይን ተከትላ አየችና ‹‹ያምሻል እንዴ?›› ብለ በቁጣ ክንዷን ይዛት መራመድ ጀመረች፡፡ ‹‹አታፍጥጭበት እንጂ? እሱኮ ነዉ የመስሪያቤቱ ባለቤት›› ‹‹ምን?›› አለች ቤቲ በደመነፍስ የሰላምን ክንድ ተደግፋ እየተራመደች፡፡ ‹‹ሰዉዬዉ በጣም ሀይለኛ ነዉ፡፡ አፈጠጠችብኝ ብሎ ሊያባርርሽ ይችላል›› ቤቲ አይኗ ወደ መሬት አደረገች፡፡ ኮሊደሩ ረጅም ነበር፡፡ የነቤቲ ቢሮ መስፍን የቆመበት ሳይደርስ መሀል ላይ ነበር፡፡ ወደቢሯቸዉ በር ሊደርሱ ጥቂት እርምጃዎች ሲቀራቸዉ ድጋሚ ቀና ብላ ወደሱ አየች፡፡ በተለመደ የተኮሳተረ ፊቱ ሲያያት አይን ለአይን ተጋጩ፡፡ ሰላም ክንዷን እየጎተተች ወደዉስጥ አስገባቻት፡፡ ደንጋጤዋ ፍዝዝ አድርጎ አስቀመጣት፡፡ የሰላም ‹ምን ሆነሻል?› ጥያቄ እንደፈዘዘች ለመቆየት እድሉን አልሰጣትም፡፡ ከሌላ የምታዉቀዉ ሰዉ ጋር እንደተመሳሰለባት ነግራ አስተባበለችና ዝም አስባቻት፡፡ ለማሰቢያ የሚሆን ጊዜ ለማግኘት ከስራ እስከምትወጣ ለመታገስ አልቻለችም፡፡ ትንሽ ጠብቃ በሩን ከፍታ አንገቷን ብቅ አድርጋ መስፍን አለመኖሩን ካረጋገጠች በኋላ ወደመፀዳጃ ቤት ሄደችና እንዱን ክፍለ ዘግታ ተቀመጠች፡፡ መስፍን አሁንም አለቃዋ ነዉ! አሁንም በየቀኑ መገናኘት ይችላሉ ማለት ነዉ፡፡ ይሄ ነገር መጥፎ ይሁን ጥሩ አልለይ አላት፡፡ ዳግመኛ ልታገኘዉ መሆኑ ደስ ሲላት መልሶ ያስፈራታል፡፡ ያንን ግራ የገባዉ ግንኙነታቻዉን እንደገና መቀጠሉ ለራሷ ከሚፈጥርባት መዘባረቅ አልፎ ስራዋን እንዳያበላሽባት ሰጋች፡፡ ወ/ሮ ዉባለም ስለራሄል ያስጠነቀቀቻትንም አልረሳችም፡፡ ምን ማድረግ ትችላለች፡፡ የሚመጣዉን ፈርታ እጅግ በጣም የወደደችዉን ስራዋን መልቀቅ ወይስ የመጣዉ ይምጣ ብላ የሚሆነዉን መጠበቅ? ለመወሰን ገና ብዙ ማሰብ አለባት፡፡ ቀኑን መሉ ከቢሮዋ በወጣች ቁጥር ከአሁን አሁን ያገኘኛል እያለች ስትሰጋ ዋለች፡፡ ደግነቱ ሳይገናኙ ወሉ፡፡ ከስራ እንደወጣች ግን ደወለላት፡፡ ስልኩን አንስታ ድምፁን ስትሰማ መልስ ለመስጠት ጉሮሮዋ እንቢ አላት፡፡ ‹‹ስለአዲሱ ስራሽ እንኳን ደስ አለሽ ለማለት ነዉ የደወልኩት›› አላት፡፡ ‹‹አመሰግናለሁ›› አለች ከጉሮሮዋ እየታገለች፡፡ ‹‹ስራዉን ወደሽዋል? እየለመድሽስ ነዉ?›› ድምፁ በጣም የተረጋጋ መሆኑ አረጋጋት፡፡ ‹‹አዎ፤ በጣም ጥሩ ነዉ›› አለች አሁንም በትግል፡፡ድምፁ ዝም አለ፡፡ ስልኩን ከጆሮዋ አንስታ ስታየዉ አልተዘጋም፡፡ መልሳ ጆሮዋ ላይ አድርጋ መጠበቅ ያዘች፡፡ ድምፁ ሲጠፋባት ‹‹ሄሎ›› አለች መኖሩን ተጠራጥራ፡፡ ‹‹አለሁ›› አላት፡፡ እሱም የሚናገረዉ እንደጠፋበት ገመተችና ‹‹ስራዉን በጣም ወድጄዋለሁ፡፡ ለኔ ከሚገባዉ በላይ ነዉ፡፡ በጣም ነዉ የማመሰግንህ›› አለችዉ፡፡ ‹‹ምንም አይደለም፡፡ ስራዉን የተቀጠርሽዉ የትምህርት ደረጃሽ ስለሚመጥን መሆኑን አትርሺ፡፡ ከዚህ በኋላ ደግሞ ለመልመድ የራስሽን ጥረት ማድረግ ይኖርብሻል›› ‹‹እሺ፡፡ ግን አንተ ነህ ይህንን እድል የሰጠኸኝ፡፡ እንደማላሳፍርህ ተስፋ አድጋለሁ›› አለችዉ; ከልቧ ነበር፡፡ ‹‹እኔም›› ሲል መለሰ፡፡ ቀጥላ የምትናገረዉ ነገር አልነበራትም፡፡ እሱም ትንሽ ዝም ብሎ ከቆየ በኋላ ስልኩን ዘጋዉ፡፡
ቤቲ በሚቀጥሉት ቀናቶች መስፍንን አላገኘችዉም፡፡ ብታገኘዉም ግን አሁን ዝግጁ ስለነበረች እንደማትደነግጥ አምናለች፡፡ ስራዋን በትኩረት ለመስራት በጣጣር ላይ ነበረች፡፡ ብቃቷን ለማሳየት ቆርጣ ተነስታለች፡፡ አሁን ስራ ከጀመረች ሳምንት አለፋት፡፡ ከሰላምም ሆነ ከወ/ሮ አለምፀሀይ ጋር ጥሩ ከመግባባታቸዉም አልፈዉ ስራዉንም መስሪያቤቱንም በደንብ ለምዳለች፡፡ ከስራ ሰአት ቀድማ ገብታ እስኪመሽ ሰርታ እንኳ አይደክማትም፡፡ ካማረ ቢሮዋ ወጥታ ያማረ ቤት መግባቷ በየቀኑ አምላክን እንድታመሰግን አድርጓታል፡፡ ያስጨንቃት የነበረዉ አንድ ነገር ብቻ ነበር፡፡ እሱንም ቢሆን ለጊዜዉ ተወት አድርጋዋለች፡፡ መስፍን ከዚያ ቀን በኋላ በስልክም በአካልም ስላላገኘችዉ በትንሹ ተረጋግታለች፡፡ ምንም እንኳ ስለሱ ማሰቧን ባታቆምም ስራዋ የማሰቢያ ጊዜ ስላሳጣት ደስ ብሏታል፡፡ ስራዋ መሸሸጊያ ሆኗላታል፡፡ ግን ይሄ መረጋጋት ብዙ አልቆየም፡፡ አንድ ቀን እንደተለመደዉ ስራዋ ላይ ተጠምዳ ቆይታ ሰራተኛ ከዉጣ በኋላ ቢሮዋ ቀርታ የቀረ ስራ በማጠናቀቅ ላይ እንዳለች ያልጠበቀችዉ እንግዳ ከች አለባት፡፡ ራሄል ነበረች! ገና ስታያት በተቀመጠችበት ዉሀ ሆነች፡፡ ራሄል ገብታ በሩን ከዘጋች በኋላ ወደጠረጴዛዋ ስትራመድ የሂል ጫማዋ ‹ቋ..ቀጭ ›የሚል ድምፅ እንደተተኮሰ ሽጉጥ ድምፅ ያክል አስፈራት፡፡ ጠረጴዛዉን ደገፍ ብላ በአንድ ጎኗ ተቀመጠችና ‹‹እሺ እመቤቲቱ›› አለችት በፌዝ ቃና፡፡ ቤቲ እጆቿን ወደራሷ ሰብስባ ሰይጣን እንዳየ ሰዉ ፊቷ ጠቁሮ በድንጋጤ ቀና ብላ ታያታለች፡፡ ‹‹ደሞ እዚህ ምን ልትሰርቂ መጣሽ?›› ቤቲ መልስ ለመስጠት አልደፈረችም፡፡ ‹‹ከቤት ስትባረሪ በኔ ዙሪያ ድርሽ እንዳትይ ዉቤ አልነገረችሽም እንዴ?እ?›› ቤቲ እየተርበተበተች ‹‹እኔ.. እኔ..›› ብቻ ነበር ማለት የቻለችዉ፡፡ ‹‹እንቺ ምን? አንቺ ማለት ተራ የፅዳት ሰራተኛና ሌባ ብቻ ነሽ! እንዳንቺ አይነት ሰዉ እዚህ ቦታ መቀመጥ አይገባዉም›› ፊቷ ላይ ያለዉ ንቀትና ጥላቻ ቤቲን መግቢያ አሳጣት፡፡ ‹‹ትሰሚኛለሽ…›› ስትል ቀጠለች ራሄል ‹‹ባሌን ምን ብለሽ እንዳሞኘሽዉ አላዉቅም፡፡ እኔን ግን አታሞኝኝም፡፡ ልክ ከቤቴ ዉልቅ ብለሽ እንደወጣሽዉ ከዚህ መስሪያቤትም ዉልቅ ብለሽ ትወጫለሽ፡፡ የታገስኩሽ አሳዝነሽኝ ነበር፡፡ አንቺ ግን መታዘን አይገባሽም፡፡ ከዚህ በኋላ ባሌ ባለበት ቦታ እግርሽ ቢረግጥ ያንን አጭበርብረሽ ያገኘሽዉን ቤት ብቻ ሳይሆን ብዙ ነገርሽን ታጫለሽ፡፡ የምልሽ ይገባሻል?›› ቤቲ አሁንም እንደደነዘዘች ታያታለች፡፡ ራሄል ከጠረጴዛዉ ላይ ተነስታ አንድ ጊዜ ከገላመጠቻት በኋላ ከከፍሉ ወጣች፡፡ ቤቲ ልክ ታፍኖ እንደቆየ ሰዉ ቁና ቁና ተነፈሰች፡፡ ተነስታ ክፍሉ ዉስጥ እየተንቆራጠጠች አሁንም ደግማ ደጋግማ ተነፈሰች፡፡ ፍርሀቷ እስኪበርድ ድረስ ተነፈች፡፡
2 ቤቲን ስራ ማስቀጠሩ ለሱ ቀላል ነበር፡፡ ከቤቱ ዉጭ ለሱ ቀርብ ቦታዉ ድርጀቱ ነዉ፡፡ የድርጅቱ ሰራተኛ እስከሆነች አሁንም በቅርብ ሊያገኛት ይችላል፡፡ ለራሱ በግልፅ አምኖ ባይቀበለዉም አሁንም በቁጥጥሩ ስር መሆኗ አስደስቶታል፡፡ ስራ ቦታ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያያት የተሰማዉ ስሜት የተለየ ነበር፡፡ ድጋሚ ሊያገኛት መሆኑ ሲያስደስተዉ የለበሰችዉ አለባበስና ጠቅላላ ሁኔታዋ ደግሞ ልክ ለመጀመሪያ ጊዜ ያያት ሴት ላይ በመማረክ ላይ እንዳለ እንዲሰማዉ አድርጎታል፡፡ ረጅም ፀጉሯ ጀርባዋ ላይ ተበትኖ፤ ከላይ ያደረገችዉ ነጭ ሽሚዝ ዉበቷን አፍክቶት፤ ከስር የለበሰችዉ ጉልበቷ ለይ የሚያበቃ ጥቁር ጉርድ ቀሚስ ወገቧን አቅጥኖ ዳሌዋን አስፍቶ ፤ በዛ ላይ የባቷ እንከን የለሽ አቀማመጥ ከሂል ጫማዋ ጋር ተደምሮ ሲያያት ያች በሽርጥ የሚያዉቃት ሴት አልመስልህ አለችዉ፡፡ ናፋቆት ጉጉትና ወንድነቱ አብረዉ ፈተኑት፡፡ ግን አሁን ከዚህ በፊት እንዳደረገዉ ዘሎ ሊያንቃት አልፈለገም፡፡ የምትረጋጋበት ጊዜ ሊሰጣት ይገባል፡፡ ከዚያ ደግሞ ሳትሳቀቅ ሊያናግራት የሚችልበት ቦታ ሊወስዳት ይችላል፡፡ እስከዛ ድረስ ግን እሱ ራሱ የራሱን ስሜት በመቆጣጠር ከሷ እየፈለገ ያለዉን ነገር በግልፅ ለመረዳት ሞመከር አለበት፡፡
ችግሩ የቤቲን ወደሱ መቅረብ ደስታ እንዳያጣጥም የሚያደርጉ ሌሎች ነገሮች ነበሩ፡፡ ከአቶ መኮንን ጋር የገባዉ አዲስ ዉል ከቀን ወደቀን እያሳሰበዉ መጥቷል፡፡ እስካሁን ያፈረሳቸዉ ቤቶች እንዳያንሱት አሁንም ለሌሎች ቀጣይ ግንባታቸዎች እየመረጣቸዉ ያሉት ቦታዎች ተመሳሳይ ነበሩ፡፡ ያ ማለት በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ያፈናቅላል ማለት ነዉ፡፡ በዛ ላይ የካሳ ገንዘቡን እስካሁን በሰበብ አስባብ እየከፈለ አይደለም፡፡ አቶ መኮንን እያደረገ ያለዉ ነገር ወደበጎ እንደማይሄድ መስፍን ታዉቆታል፡፡ ግን እንዴት ይሄንን ሰዉ እንደሚያስቆም ወይም እራሱን ከዚህ ፕሮጀክት እንደሚያወጣ ሊታየዉ አልቻለም፡፡ በዚህ በተጋጋለ ዉጥረት ዉስጥ ሆኖ ነበር ራሄል እየተወራጨች ቤቱ ወደሚገኘዉ የቢሮ ክፍሉ የገባችዉ፡፡ ገና የክፍሉን በር ከፍታ ስትገባ የመጣችዉ በደህና እንዳልሆነ ገብቶታል፡፡ ‹‹ምንድነዉ አሁን ደግሞ?›› አለ በስልችት፡፡ ‹‹ያችን ልጅ ከዚህ ስትባረር ብለህ ብለህ ድርጅቱ ውስጥ ቀጠርካት አይደል? ቆይ አንተ ምንድነዉ ከሷ ጋር ያለህ? በከተማዉ ላይ ደህና ሴት ጠፍቶ ነዉ? ሰዉስ ምን ይልሀል? የፅዳት ሰራተኛህን ማናጀር ቢሮ ዉስጥ የቀጠርካት ምን እንድትሰራ ነዉ? መወልወያና መጥረጊያ እንድታስተዳድር? እ? እኔ ያንተ ነገር በጭራሽ አልገባ ብሎኛል መስፍን፡፡ ሌላ ሴት መወሸም አንድ ነገር ነዉ፤ ከእንዲች አይነት ተራ ሴት ጋር አልላቀቅም ማለት ምን ይሉታል? ለኔ ባታስብ ለክብርህ አታስብም እንዴ?›› ወርጅብኟን ከጩኸትና ከብዙ መወራጨት አወረደችበት፡፡ በፍቅር ስታናግረዉ የቆየች ይመስል በተረጋጋ ድምፅ ‹‹ከዚህ ቤት አንች ነሽ ያባረርሻት?›› አላት፡፡ ‹‹ምን?›› አለች በግርምት ‹‹እሱ ነዉ አንተን የሚያሳስብህ?›› ‹‹ጥያቄዬን መልሽልኝ?›› አላት አሁንም በእርጋታ ‹‹ አዎ እኔ ነኝ! ምን ጠብቀህ ነበር? ባሌን ስላማገጥሽልኝ አመሰግናለሁ ብዬ እንድሸልማት? ጤነኛ አይደለህም እንዴ›› ‹‹ራሄል›› አለ መስፍን ‹‹አየሽ ይሄ ባህሪሽ ነዉ ካንቺ ያስራቀኝ፡፡ ሁሌም አንቺ ገንዘብ ስላለሽ ብቻ ታላቅ ሰዉ የሆንሽና የተቀረዉን ሰዉ እንደፈለግሽ ማድረግ እንደምትችይ ታስቢያለሽ፡፡ ልጅቷ ደሀ ስለሆነች ብቻ የፈለግሽዉን ብታደረጊያት ምንም ማድረግ እንደማትችል ስለምታዉቂ ያለሽን ሀይል በሙሉ ተጠቅመሽ ህይቷን ብታበላሺ ደስ ይልሻል፡፡ አንቺና አባትሽ ደስታ የምታገኙት ከሰዉ ስቃይ ነዉ፡፡ ጨካኝ ሰዉ ነሽ ራሄል…ጨካኝ›› ከንግግሩ በላይ ፊቱ ላይ የሚታየዉ ጥላቻ ብዙ ይናገር ነበር፡፡ ‹‹እሺ የኛ መልአክ!›› አለች በፌዝ ‹‹አንተስ ሚስትህ ላይ መማገጥህ ምን ያስብልሀል? ንገረኝ እስኪ›› ‹‹እኔ›› አለ የምፀት ፈገግታ ፈገግ ብሎ ‹‹እኔ ኑሮ ከእንዳንቺ አይነት ልብ የሌላት ፍቅር የማታዉቅ ቀዝቃዛ ሴት ጋር መኖር የመረረዉ ወንድ ነኝ›› ‹‹ምን አልክ?›› አለች ፊቷ በአንዴ እየተለወጠ፡፡ ‹‹ይሄ ትዳር በቅቶኛል ራሄል፡፡ በርግጥ ትዳራችን… ትዳር ከተባለ… ካከተመ ቆይቷል፡፡ አሁን ግን በቃኝ››፡፡ ራሄል አንገቷን ለመንቃት ያህል አነቃነቀችና ‹‹ምን እያልከኝ ነዉ መስፍን?›› አለችዉ፡፡ ‹‹ፍቺ እፈልጋለሁ!››፡፡ ከት ብላ ሳቀች፡፡ ሳቋ የሚያስፈራ የእበደት ሳቅ ነበር፡፡ ‹‹ተዉ አታስቀኝ›› አለች ሳቋን ገታ አድርጋ ‹‹ማንን እያናገርክ እንደሆነ ረሳኸዉ መሰለኝ፡፡ እኔኮ ራሄል መኮንን ነኝ›› ከተቀመጠበት ተነስቶ ኮቱን እየደረበ ‹‹አዎ ነሽ›› አላት፡፡ ‹‹እኔም መስፍን ዉብሸት ነኝ›› ይህንን ተናግሮ መልሷን ሳይጠብቅ ከቤት ወጣ፡፡
ምንም ያክል ቢናደድም በመጨረሻ ስሜቱን መናገሩ እፎይታ ሰጥቶታል፡፡ ለአመታት ከታሰረበት የይስሙላ ትዳር ለመዉጣት መድፈሩና አዲስ ሂወት ለመጀመር በመቁረጡ በራሱ ረክቷል፡፡ በቀጥታ የሄደዉ አልፎ አልፎ የሚሄድበት አንድ ሆቴል ነበር፡፡ ወደቤት ለመመለስ እቅድ ስላልነበረዉ አልጋ እዛዉ ይዞ የባሩ ባልኮኒ ጋር ተቀምጦ መጠጡን ተያያዘዉ፡፡ እየተሰማዉ ያለዉ ነፃነት የተለየ ነበር፡፡ ይህን ስሜት ካገባ ጀምሮ አይቶት አያዉቅም፡፡ ገና ልጅ ገና ወጣት ሆኖ ስለህይወት የነበረዉ ጉጉት ድጋሚ አደረበት፡፡ ስሜቱን እያጣጣመ እንዳለ አዲሱ ስለደወለለት ያለበትን ነገረዉና ‹ተቀላቀለኝ› አለዉ፡፡ አዲሱ ሲመጣ መስፍን ገና ሞቅ ሊለዉ ጀምሯል፡፡ ከራሄል ጋር የተፈጠረዉን በአጭሩ ነገረዉና ዛሬ የደስታ ቀኑ እንደሆነ አበሰረዉ፡፡ አዲሱ ሁኔታዉ ባያምረዉም አልተቃወመዉም፡፡ ፊት ለፊት ተቃዉሞ የትም እንደማያደርስ ያዉቃል፡፡ እንዲያዉም አብሮት እየጠጣ እያሳሳቀዉ ብርጭቆ ሲያጋጩ አመሹ፡፡ መስፍን እየተዳከመ ሲመጣ ወደ አልጋ ክፍሉ ገባ፡፡ በወደቀበት ሳይገላበጥ ነበር ያደረዉ፡፡ በማግስቱ አረፋፍዶ ራሄልን ማግኘት ባይፈልግም ልብስ መቀየር ስለነበረበት ወደቤቱ ሄደ፡፡ ደግነቱ ራሄል ቤት አልነበረችም፡፡ ጭራሹንም እቤት አለማደሯን ሲነገረዉ የት እንዳደረች ከጉዳይም ሳይቆጥረዉ ልብሱን ቀይሮ ወደ ስራ ወጣ፡፡ ቢሮ እንደገባ ግን አዲሱ ፊቱን አጥቁሮ እንግዳ ወንበሩ ላይ ተቀምጦ ጠበቀዉ፡፡ ‹‹ ሰላም አይደለም?›› አለዉ ገና እንዳየዉ፡፡ ‹‹ቁጭ በል እስኪ›› አለ አዲሱ፡፡ ሁኔታዉ መርዶ ሊያረዳ የመጣ ሰዉ አስመስሎታል፡፡ መስፍን ወንበር ላይ አረፍ አለና ‹‹ችግር አለ?›› ሲል ጠየቀዉ፡፡ ‹‹መስፍን… ምን ብዬ እንደምነግርህ አላዉቅም… ግን… በጣም ከባድ ችግር አጋጥሞናል›› ‹‹ምንድነዉ? መኮንን ነዉ አይደል? አሁን ደግሞ ምን አደረገ?›› አለ መስፍን በቁጣ፡፡ ‹‹ከዚህ በፊት በንዴት ያስገባኸዉን የዉል ማቋረጫ ተቀብሎሀል››፡፡ መስፍን ትንሽ ግራ በመጋባት አሰብ አደረገና ‹‹እንዴት? ለምን ያን ጊዜ ያልተቀበለዉን ዉል አሁን ተቀበለዉ? በዛ ላይ ዉሉ ቀኑ ስላለፈ አሁን አያገለግልም›› ፡፡ ‹‹ራሄል የሆናችሁትን ሳትነግረዉ አትቀርም›› አለ አዲሱ አሁንም በጭንቀት ተዉጦ፡፡ ‹‹ባለፈዉ ያስገባሁት ዉል ጊዜዉ ስላለፈ አሁን አያገለግልም፡፡ በእርግጥ ግን ለልጁ ተደርቦ ዉሉን ለማቋረጥ ከፈለገ እኔ ያለምንም ቅደመሁኔታ እስማማለሁ›› አለ መስፍን ፈገግ እያለ፡፡ ‹‹እሱ ነዉ ችግሩ መስፍን፡፡ ያስገባኸዉ የዉል ማፍረሻ ላይ የቀን ገደብ አላስቀመጥክም፡፡ ወረቀቱ ደግሞ አሁንም በእጃቸዉ ይገኛል›› ‹‹ምን እያልከኝ ነዉ?›› አለ መስፍን አይኑን አጥብቦ እየተመለከተዉ፡፡ ‹‹በሰአቱ ተናደህ ስለነበር የዉል ማፍረሻዉን በጥንቃቄ አላዘጋጀኸዉም፡፡ አሁን አቶ መኮንን ዉል ማፍረሻዉን ተቀበለህ ማለት ፕሮጀክቱ ላይ ያፈሰስከዉን ንብረት ታጣለህ ማለት ነዉ›› መስፍን በዝምታ ነገሩን ማጤን ጀመረ፡፡ ‹‹ይሄ ብቻ አይደለም›› አለ አዲሱ ‹‹ከራሄል ጋር ለመፋታት ከወሰንክ ግማሽ ንብረትህን ትካፈልሀለች ማለት ነዉ›› ‹‹የራሷ በቂ ንብረት አላት፡፡ ከኔ ምን ትፈልጋለች?›› አለ መስፍን በቁጣ፡፡ ‹‹ዛሬ ጠዋት ከራሄልና ከአባቷ ጋር ባደረኩት ንግግር እንደተረዳሁት ራሄል በስሟ የተመዘገበ አንድም ንብረት የላትም፡፡ ስትጋቡ የነበራትን ንበረት በሙሉ በአባቷ ስም አዙራለች›› ‹‹ምን?›› ሲል አንባረቀ፡፡ ‹‹መስፍን እባክህ ተረጋግተህ ስማኝ›› አለ አዲሱ በልመና ድምፅ ‹‹አሁን ለንዴት የሚሆን ጊዜ የለም›› ‹‹ምን ማለትህ ነዉ? አሁን ካልተናደድኩ መቼ ልናደድ? ይቺ ጭራቅ ይሄን ሁሉ ጊዜ እንዴት እንደምታርደኝ ስትዘጋጅ ነበር የኖረችዉ ማለት እኮ ነዉ! ከዚህ በላይ ምን አለ›› ‹‹ከዚህ በላይ የሚያስጨንቀዉማ አቶ መኮንን ፕሮጀክቱ ላይ ያፈሰስከዉን ገንዘብ ጠቅልሎ ከወሰደዉና ሚስትህ ግማሽ ንብረትህን ከወሰደችዉ የሚቀርህ የባንክ እዳ ብቻ መሆኑ ነዉ›› ሲል አዲሱ መልሶ አንባረቀበት፡፡ መስፍን ሚናገረዉ ስላጣ ከተቀመጠበት ተነስቶ ክፍሉ ዉስጥ ይንጎራደድ ጀመር፡፡ ትንሽ ዝም ተባብለዉ ቆዩና አዲሱ ‹‹ግን ሁሉም ነገር የሚስተካከልበት አንድ ማራጭ ራሄልና መኮንን ሰጥተዉናል›› አለ፡፡ መስፍን አማራጩ ጥሩ እንደማይሆን ስለገባዉ የንዴት ሳቅ ሳቀና ወደአዲሱ ዞር አለ፡፡ ‹‹ከራሄል ጋር ትዳሩን የምትቀጥል ከሆነ መኮንን ዉሉን ለማፍረስ ያቀረብከዉን ዉል ዉድቅ ያደርገዉና ፕሮጀክቱ ይቀጥላል›› መስፍን ዝም ብሎ ሲያየዉ ንግግሩን ቀጠለ፡፡ ‹‹ራሄል አንዳነድ የመደራደሪያ ነጥቦች አቅርባለች፡፡ በሀሳቡ ከተስማማህ ዝርዝር ጉዳዮቹ ላይ የምትነጋገሩ ይሆናል››፡፡ መስፍን መንጎራደዱን ቀጠለ፡፡ ረዘም ላለ ደቂቃ ሲንጎራደድ ቆየና ‹‹መኮንን ሁሌም ሰዉ እንዴት ጠልፎ መጣል እንዳለበት የሚያዉቅ ሰዉ ነዉ፡፡ ምንም ነገር ሲሰጥህ እንዴት በኋላ እንደሚቀበልህ ሳያዉቅ አይሰጥህም፡፡ አሁንም ይሄን ምርጫ የሰጠኝ በመያዣ ነዉ፡፡ እርግጠኛ ነኝ ይህንን ምርጫ ሲያቀርብልህ የዉል ማፍረሻዉን እመልሳለሁ አላለህም፡፡ ያ ማለት ዉል ማፍረሻዉ የቀን ገደብ ስለሌለዉ በማንኛዉም ሰዐት ሊጠቀምበት ይችላል ማለት ነዉ፡፡ እነዚህ ሰዎች በትዳርም በስራም አስረዉ ሊይዙኝ ነዉ እቅዳቸዉ›› አለ አይኑ ደም ለብሶ፡፡ ‹‹መስፍን አሁን ግን ሌላ አማራጭ የለህም፡፡ ባቀረቡት ሀሳብ ተስማማ፡፡ ቀስ ብለህ ነገሮች ሲረጋጉ እንዴት ከዚህ ነገር እንደምትወጣ ብታስብበት ይሻላል›› አለ አዲሱ በልምጥ፡፡ ‹‹አሁን ብቻዬን መሆን እፈልጋለሁ›› አለ መስፍን፡፡ ‹‹እሺ፤ ግን እባክህ ተረጋግተህ አስብ›› አዲሱ እያመነታ ከቢሮዉ ወጣ፡፡
መስፍን አይምሮዉ ላይ ብዙ ነገር ተመላለሰበት፡፡ ራሄል በንዴት ያደረገችዉ ነገር ቢሆን አይገርመዉም ነበር፡፡ ግን ስትዘጋጂበት የቆየችዉ ነገር መሆኑ አንገበገበዉ፡፡ ከዚች ሴት ጋር ከዚህ በኋላ አንዲት ቀን እንኳ እንዴት አብሯት ያድራል? ግን ደግሞ ሀብቱን በሙሉስ ሲያጣ እንዴት ዝም ብሎ ያያል? በዚህ ሁሉ ዉጥረት ዉስጥ ግን ቤቲ ንጹህና ከክፋት የጠራች ሆና ታየችዉ፡፡ ከራሄልና ከአቶ መኮንን ሰይጣናዊነቲ መሀል የምታበራ መልአክ መሰለችዉ፡፡ አሁን የምታስፈልገዉ እሷ ናት፡፡ እሷ ብቻ ናት የምታረጋጋዉ፡፡ ማሰብ የሚችለዉ እሷን ካገኘ ነዉ፡፡ ስልኩን አንስቶ ደወለላት፡፡ ስልኩ ተነስቶ ‹‹ሀሎ›› የሚለዉን ድምጽ ሲሰማ ገና መንፈሱ ሲቀያየር ታወቀዉ፡፡ ‹‹ቤዝመንቱ ዉስጥ ያለዉ ስቶር በአምስት ደቂቃ ዉስጥ እንድትመጭ!›› ትንሽ ዝም ብላ ቆየችና ‹‹እሺ›› አለችዉ፡፡ ስልኩን ዘግቶ እየተጣደፈ ከቢሮዉ ወጣና ሊፍት ዉስጥ ገብቶ ወደ ሁለተኛዉ አንደር ግራዉንድ ሄደ፡፡ የመጋዘኑን ጠባቂ ሻይ እንዲጠጣ ከላከዉ በኋላ በተደራረቡ ካርቶኖች በተከበበዉ ሰፊ ክፍል ዉስጥ እየተንጎራደደ መጠበቅ ያዘ፡፡ አመታት የጠበቀ እየመሰለዉ በጉጉት ሲንቆራጠጥ የእርምጃ ድምፅ ስለሰማ ወደበሩ ሲዞር ቤቲ የክፍሉን በር አልፋ ስትገባ አያት፡፡ ሰማያዊ ጉርድ ቀሚስ በጥቁር ስስ አላባሽ ለብሳለች፡፡ ፀጉሯ እንደባለፈዉ ትከሻዋ ላይ ተበትኗል፡፡ ክፍሉ መሀል ላይ ስትደርስ ቆም አለች፡፡ እየተንደረደረ መጥቶ አቀፋት፡፡ እጆቿ ወደታች እንደተንጠለጠሉ ዝም ብላ ታቀፈችለት፡፡ ጭምቅ አድርጎ አቀፋትና ለቀቅ አድሮጎ ፊቷን በፍቅር ከተመለከተ በኋላ ከንፈሯን በስሱ ሳም አደረገዉ፡፡ ቀና ብሎ ሲያያት አይኖቿ ተጨፍነዋል፡፡ እንደገና ከንፈሯን ግጥም አድርጎ ሳማት፡፡ አሁን ግን አላቆመም፡፡ በሀይል ይመጣት ጀመር፡፡ ባልጠበቀዉ መልኩ እሷም መልሳ ስትሰመዉ ተሰማዉ፡፡ እጆቿ አሁን በወገቡ ዙሪያ አቅፈዉታል፡፡ የእሱ እጆች ከአንገቷና ከትከሻዋ ወርደዉ ወደወገቧ ሲወርዱ የሷ እጆች ደግሞ በተራቸዉ ወደአንገቱና ወደጀርባዉ ወጡ፡፡ አንዳቸዉ በእንዳቸዉ ከንፈር ዉስጥ ሰመጡ፡፡ ለአፍታ እንደቆዩ ግን እጆቿ ደረቱን ይዘዉ ሲገፉት ታወቀዉ፡፡ ወደኋላ ሸሸት ብሎ አያት፡፡ ‹‹ተወኝ›› አለችዉ እንባ ባዘሉ አይኖች እያየችዉ፡፡ ‹‹እባክህ ተወኝ››፡፡ አይኖቿ ሲጨፈኑ ወፍራም የእንባ ዘለላዎች ጉንጮቿ ላይ ከብለል አሉ፡፡ በሀዘኔታ ካያታ በኋላ አይኖቹን ጨፍኖ በግንባሩ ግንባሯን ተደገፈ፡፡ ‹‹አልቻልኩም›› አለ በቀስታ ‹‹አልችልም፡፡ ልተዉሽ አልችልም›› እንባ ያራሰዉን ጉንጯን ሳማት፡፡ ሸሚዙን ጨምድዳ በሁለት እጆቿ ከያዘች በኋላ ባለ በሌለ ጉልበቷ ስትገፈትረዉ ወደኋላዉ ተንገዳግዶ ቆመ፡፡ በድንጋጤ አፍጥጦ አያት፡፡ ፊቷ ላይ አይቶት የማያዉቀዉ ንዴት ተመለከተ፡፡ ‹‹ምንድነዉ ከኔ የምትፈልገዉ?›› አለች ከፍ ባለ ድምጽ፡፡ ‹‹አንተ ማንም ሴት የምትፈልግህ ሀብታም ወንድ ነህ፡፡ እኔ ምንም የሌላት አንድ ተራ ሴት ነኝ፡፡ ለምን ታሰቃየኛለህ? ትወደኛለህ እንዳልል ትጠላኛለህ እንዳልል አድርገህ ለምን መሀል ላይ ታንገላታኛለህ? ከሚስትህ ማስፈራሪያ በላይ አንተን መዉደዴ እንዴት እንደሚያስፈራኝ ታዉቃለህ? ባለትዳር ወንድ መመኘቴ የገዛ ህሊናዬን ምን ያህል እንደሚቆረቁረኝ ታዉቃለህ? እንደአንተ አይነት ወንድ እንደኔ አይነት ሴት ይወዳል ብዬ ማሰቤ በራሱ ምን ያህል እንደሚያሳፍረኝስ ታዉቃለህ?›› የንግግሯ ለዛ ከማሳዘኑም በላይ አንጀት ይበላል፡፡ ‹‹ ትወጅኛለሽ?›› አላት በዝግታ ወደሷ እየተራመደ፡፡ መልስ አልሰጠችዉም፡፡ ‹‹እኔስ ምን ያህል በፍቅርሽ እየተሰቃየሁ እንደሆነ ታዉቂያለሽ? እያስገደድኩሽ እንዳለ ሲሰማኝ ምን ያህል እንደምሸማቀቅ ታዉቂያለሽ?››፡፡ አሁን አጠገቧ ደርሷል፡፡ መዉደዱን ሲናዘዝ ለመጀመሪያ ጊዜ መስማቷ ነዉ፡፡ እወድሻለሁ ሲላት የሰማችዉ እዉነት መሆኑን ባለማመን ፈዛ ቀርታለች፡፡ ተጠግቷት ሲቆም ዉስጧ ያለዉን ጉልበት ሁላ ተጠቅማ አቀፈችዉ፡፡ አሁን የምትፈራዉ ነገር አልነበራትም፡፡ ከሱ የሰማችዉ የፍቅር ቃል ምንም ነገር ማንንም ሰዉ እንዳተፈራ ድፍረት ሰጣት፡፡ በመልሱ መልሶ ሲያቅፋት ሲስማት እጆቹ መላ ሰዉነቷ ላይ ሰተራመሱ አላስቆመችዉም፡፡
ሁሉንም ነገር ድጋሚ በማድረግ ላይ ነዉ፡፡ ቤቱ የወሰዳቸዉን ዶክመንቶች ደጋግሞ አገላበጠ፡፡ መስሪያ ቤቱ ዉስጥ ያለዉን ፋይል በድጋሚ አጣራ፡፡ ምንም የለም፡፡ ተስፋ ሊቆርጥ ትንሽ ሲቀረዉ ግን ያልጠበቀዉ ጥሪ ከአቃቢህጉ መጣ፡፡ ስልኩን አንደዘጋ ነበር ወደሱ የሮጠዉ፡፡ አቃቢህጉ የደወለበትን ምክንያት ሲያስረዳ ‹‹አንድ የአቶ መኮንን የቅርብ አማካሪ የነበረ ሰዉ ነበረ፡፡ ሰዉየዉ የሁሉም ድርጅቶች ላይ አሻራዉን ያሳረፈ ሰዉ ነዉ፡፡ ከአንድ አመት በፊት ግን በአንድ ወንጀል ተጠርጥሮ ወህኒ ወርዶ ነበር፡፡ ትላንትና እንደአጋጣሚ ፍርድቤት ሳየዉ ስላስታወስኩት የታሰረበትን ምክንያት ላማጣራት ሞክሬ ነበር፡፡ እንደሰማሁት ከሆነ ሰዉዬዉ የተወነጀለዉ በመንግስት ሀብት ምዝበራ ሲሆን ወንጀለኛ ሆኖ በመገኘቱ እስር ተፈርዶበታል›› አለ፡፡ የዚህ ሰዉ መታሰር ከእሱ ጋር ምን እንደሚያገናኘዉ ግራ የገባዉ ናትናኤል በትእግስት አፍ አፉን እያያ ጠበቀ፡፡ አቃቢህጉ ነገሩ የገባዉ ይመስል ‹‹ላንተ የደወልኩበት ምክንያት ስለሰዉዬዉ የሰማሁት ሌላ ተጨማሪ ዉስጣዊ መረጃ ስላለ ነዉ፡፡ ስለመረጃዉ እዉነትነት እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ስለዚህ ምናልባት ስህተት ሆኖ ሊገኝ ስለሚችል ብዙም ተስፋ አታድርግ፡፡ እንደተረዳሁት ከሆነ አንተ በነገሩ ተስፋ የምትቆርጥ ሰዉ ስላልሆንክ ያገኘነዉን ፍንጭ ብዙም እርግጠኛ ባይሆን እንኳ…›› እያለ ሲቀጥል ናትናኤል ትዕግስቱ አልቆ ‹‹መረጃዉን ንገረኝ፡፡ ምንም ቢሆን ለማጣራት ዝግጁ ነኝ›› አለ በችኮላ፡፡ ‹‹እሺ፤ በጣም ጥሩ!›› አለ አቃቢህጉ፡፡ ‹‹እንደሰማሁት ከሆነ ወንጀሉን የፈፀመዉ አቶ መኮንን ነዉ፡፡ የሰራዉ ሲጋለጥበት እራሱን ለማትረፍ በሚስጥራዊ ሴራ የገዛ አማካሪና ጓደኛዉ ላይ ነገሩን ጠምጥሞ እንደወነጀለዉ ነዉ የተነገረኝ፡፡ ሰዉዬዉ በጓደኝነታቸዉ ላይ በነበረዉ እምነት ተታሎ እንዳንድ ወረቀቶች ላይ ሳይፈርም አልቀረም፡፡ ታዲያ አቶ መኮንን ምንም ያክል ሰዉዬዉን ቢወደዉም በራሱ ሂወት ላመጣ ነገር ግን የብዙ አመት ባልንጀራዉን አሳልፎ ለመስጠት አላመነታም፡፡ ያዉ የአቶ መኮንን ጭካኔ እንግዲህ ለአንተ አዲስ አይደለም››፡፡ ‹‹ታዲያ ይሄ እኔን እንዴት ነዉ ሊጠቅመኝ የሚችለዉ/›› አለ ናትናኤል የነገሩ ጫፍ አልያዝ ብሎት ግራ እየተጋባ፡፡ ‹‹ይሄ እንዴት ይጠፋሀል/ እንደነገርኩህ ይህ ሰዉ ስለአቶ መኮንን የማያዉቀዉ ሚስጥር የለም፡፡ ወሬዉ እዉነት ሆኖ ከተገኘና እንደተባለዉ ይህ ሰዉ እስር ለቤት ያለዉ ባልሰራዉ ወንጀል አቶ መኮንን ባሴረዉ ሴራ ምክንያት ሆኖ ከተገኘ ይህ ሰዉዬ የሚያዉቀዉን ሚስጥር ለማዉጣት የሚያግደዉ ነገር የለም፡፡ አሁን ሄደህ ታሪክህ ብታጫዉተዉና ስለጉዳይህ የሚያዉቀዉ ነገር ካለ ብትጠይቀዉ ሰዉዬዉ በዚህ ሰአት አቶ መኮንንን ለመበቀል ብሎ የማይነግርህ ጉድ አይኖርም››፡፡ ናትናኤል የሞተ ስፋዉ በአንድ ግዜዉ አንሰራራ፡፡ አቃቢህጉን አመስግኖ ሰዉዬዉ ይገኝበታል ወደተባለዉ ወህኒ ቤት ለመሄድ ጊዜ አላባከነም፡፡
ናትናኤል ሰዉየዉን የግል ጠበቃዉ ነኝ በሚል ለብቻዉ ማንም በሌለበት የማነገሩን እድል አገኘ፡፡ የሰማዉ ትክክለኛ መረጃ ከመሆኑም በላይ ሰዉዬዉ አቶ መኮንንን ለመጣል ፍፁም ተባባሪ ነበር፡፡ ለአቶ መኮንን ለብዙ አመታት ከማገልገሉም በላይ የቅርብ ጓደኛዉ ጭምር እንደመሆኑ መጠን ስለእያንዳንዱ ድርጅት ስለተፈፀሙ ማጭበርበሮች ማን ማን እንደተሳተፈ አሳምሮ ያዉቅ ነበር፡፡ እዉቀቱ ደግሞ በማስረጃ የተደገፈ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ናትናኤል ትክክለኛ ጠላቱ አቶ መኮንን እንጂ አቶ መስፍን እንዳልሆነ አባቱ አቶ ዉብሸትም ከደሙ ንፁህ እንደነበሩ ለመረዳት በቃ፡፡ በመጨረሻ ህልሙ ተሳክቶ ጠላቱ እጁ ላይ መዉደቁን ሲያዉቅ ያደረገዉ የመጀመሪያ ነገር ለሚስኪኑ አማካሪ ሀቁን መርምሮ ነፃ እንደሚያስወጣዉ ቃል መግባት ነበር፡፡
ከአንድ ወር በኋላ በእንዱ ዉብ ምሽት ቤቴልሄም በመኝታ ቤቱ መስኮት ወደ ጊቢዉ እያየች በሀሳብ ተዉጣ ቆማለች፡፡ ዛሬ ላይ የቆመችበትን ሁኔታ ስታስበዉ ህልም ይመስላታል፡፡ ባለፉት ቀናት ነገሮች የተከናወኑት በፍጥነት ነበር፡፡ መጀመሪያ መስፍን ሚስቱና አባቷ ሚያመጡበትን መዓት ለመቀበል ዝግጁ እንደሆነና በፍፁም ከራሄል ጋር ወደትዳር እንደማይመለስ አሳወቀ፡፡ ምንም እንኳ ነገሩ በሽምግልና ለመፈታት ቢሞከርም የሚሳካ አልነበረም፡፡ መስፍን ሁሉንም ንብረቱን ለማጣት በተቃረበበት ቅፅበት ናትናኤል በአቶ መኮንን ላይ በተገቢ መልኩ አዘጋጅቶ ያጠናቀቀዉን ክስ ይዞ ከች አለ፡፡ በጉዳዩ ላይ አቶ መኮንን ብቻ ሳይሆኑ ራሄልና አዲሱም ብዙ ተሳትፈዉበት የነበረ ሆኖ በመገኘቱ አብረዉ ተወንጅለዉ ነበር፡፡ አቶ መኮንን በቀጥታ ወደእስር ቤት ሲወረወሩ ራሄል ጨርቄን ማቄን ሳትል በፍጥነት ከሀገር በመዉጣት ሸሸች፡፡ አዲሱ ሊደርስበት ከነበረዉ የእስር ቅጣት ብዙ ወጥቶና ወርዶ ያተረፈዉ መስፍን ነበር፡፡ መስፍን አዲሱን ለቆየ ወዳጅነታቸዉ ሲል ከእስር ቢያተርፈዉም ከስራ ያባረረዉ ሲሆን ጓደኝነታቸዉም እዚሁ ላይ አከተመ፡፡ ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ ነበር መስፍን ከቤቲ ጋር ጊዜ አግኝቶ ለመዝናናት የበቃዉ፡፡
ጊቢዉን እያያች በእንድ ወቅት ለፅዳት ትመላለስበት የነበረዉ ቪላ ዛሬ እንደ እመቤት ተቆጥራ የተጋበዘችበት ቤት መሆኑ የግርምት ፈገግ አስባላት፡፡ መስፍን ከጀርባዋ መጥቶ እጆቹን በወገቧ ዙሪያ ሲጠመጥም ከነፈገግታዋ ዞር ብላ አየችዉ፡፡ የፀጉሯን ጠረን በሀይል ማግ አድርጎ ከሳማት በኋላ ‹‹አሁን አንችን ማንም አይከለክለኝም፡፡ የግሌ ሆነሻል›› አላት፡፡ ወደሱ ከዞረች በኋላ በፈገግታ እያየችዉ እጁን ይዛ እየመራች ወደአልጋዉ መራችዉ፡፡