
01/07/2025
“በኢትዮጵያ የኒውክለር ሳይንስ ላይ እየሰራን ያለነው ለሕክምና እንክብካቤ ብቻ ሳይሆን አስቀድሞ ለመቆጣጠር እና ለመከላከልም ጭምር ነው።”
የኤፌድሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
____________
የካንሰር በሽታን መከላከል እና ህክምናን ማስፋፋት ላይ ትኩረቱን ያደረገ "Rays of Hope" ተነሳሽነት አለም አቀፍ ጉባኤ በዛሬው ዕለት መካሄድ ጀመረ።
ከተለያዩ አፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ሚኒስትሮችን እና አምባሳደሮችን ያሰባሰበው ይህ አለም አቀፍ ጉባኤ በጤና ሚኒስቴር እና በአለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ (አይኤኢኤ) በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን፤ የIAEA "Rays of Hope" ተነሳሽነት አባል ሀገራት የኢሜጂንግ፣ የኒውክለር ህክምና እና የራዲዮቴራፒ ህክምናን በማስፋፋት የአገልግሎቶችን ተደራሽነት ለማሻሻል እንዲሁም ይህ የህይወት አድን ህክምና በሌላቸው ሀገራት ላይ የህክምና አገልግሎት እንዲጀመር ድጋፍ ለማድረግ ኢላማ አድርጎ የተመሰረተ ተነሳሽነት(initiative) ነው።
በጤናው ዘርፍ ብዙ ህይወት አድን ቴክኖሎጂዎችን ለማምጣት መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በጉባኤው የመክፈቻ ንግግራቸው የገለፁ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ የሬዲዮቴራፒ ህክምናን ከማስፋፋት በተጨማሪ የኒውክለር ሳይንስ ላይ እየተሰራ ያለው ለሕክምና እንክብካቤ ብቻ ሳይሆን አስቀድሞ ለመቆጣጠር እና ለመከላከልም እንደሆነ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የካንሰር ህክምና ማዕከሎችን በክልሎችም ጭምር እያሰፋች መሆኗን የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በመድረኩ ገልጸው፤ አምስት አዳዲስ የክልል ማዕከላት መከፈታቸውን እና ይህም ቀደም ሲል በአዲስ አበባ ብቻ ተወስኖ የነበረውን አገልግሎት ተደራሽነትን የጨመረ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የIAEA "Rays of Hope" ተነሳሽነት የራዲዮቴራፒ አገልግሎቶችን፣ የህክምና ምስል (ኢሜጂንግ) እና የኒውክሌር ህክምና አቅርቦትን በማሻሻል የካንሰር ህክምና ተደራሽነትን በተለይም ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ለማስፋት ያለመ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአለም አቀፍ የኑውክለር ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ግሮሲ፤ ተነሳሽነቱ የካንሰር ህክምና ባልተስፋፋባቸው ከ20 በላይ የIAEA አባል ሀገራት የራዲዮቴራፒ አገልግሎቶችን መመስረት እና ማስፋፋትን ይደግፋል ብለዋል።
በአለም አቀፍ ጉባኤው ኢትዮጵያ የካንሰር ህክምናን ለማስፋፋት እያደረገች የምትገኘውን ጥረት የገለጹት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ፤ ጤና ሚኒስቴር ከIAEA "Rays of Hope" ተነሳሽነት ጋር በቅርበት በመስራት የካንሰር ህክምናን በኢትዮጵያ ለማስፋፋት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ የሰባት የአፍሪካ ሃገራት የጤና ሚኒስትሮች መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን በIAEA እና በሴንት ጁድ የህጻናት ህክምና ምርምር ማእከል የመግባቢያ ስምምነት ተፈርሟል፡፡
Website: moh.gov.et
Facebook: Ministry of Health,Ethiopia
Twitter: x.com/fmohealth
YouTube: youtube.com/
Tiktok: tiktok.com/
Telegram: t.me/M0H_EThiopia