17/05/2025
የህክምና ባለሙያዎች ጥያቄ የመኖር እንጂ የስልጣን ጥያቄ አይደለም።
ቆይ እኔ የምለው፣ የሆነ የማትወዱት ፖለቲከኛ ሀሳቡን ስለደገፈው ብቻ ጥያቄው ልክ አይደለም ማለት ነው? ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ነገር ትክክል የሚባለው የናንተ ሰው ሲናገረው ብቻ ነው? እውነትና ፍትህ ያለማንም የቃል-ባላ በራሳቸው መቆም ይችላሉ። በቃ፣ ለዳቦ ጥያቄ መልሱ "ዳቦ" ነው።
"እዚህ አሜሪካን" እያልኩ ላዝግህ ባልፈልግም "እዚህ አሜሪካን" ከፍተኛ ክፍያ የሚከፈላቸው አስር ስራዎች ብለህ ብትጎግል የምታገኘው መልስ Neurosurgeons ($239,200+), Chief Executive Officers (CEOs) ($350,000–$1,500,000), Pediatric Surgeons ($239,200+), Cardiologists ($423,250), Anesthesiologists ($239,200+), Orthopedic Surgeons (Except Pediatric) ($239,200+), Dermatologists ($342,860), Radiologists ($239,200+), Surgeons, All Other ($239,200+), Oral and Maxillofacial Surgeons ($239,200+).... ወደ ብር ልቀይረው?
አየህ ከአስሩ ዘጠኙ የህክምና ባለሙያዎች የሆኑበት ምክንያት አለው። ጎረቤት ኬንያ (ያውም አነሰ፤ ሰልፍ እንወጣለን እያሉ) ለአንድ ዶክተር በዓመት ከ34,000 ዶላር በላይ ደሞዝና ጥቅማጥቅም ስትከፍል ምክንያት አላት። ተወው አሜሪካን፣ ተወው ኬንያንም፣ ከዛሬ ነገ ፈረሰች አልፈረሰች የምንላት ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ መንግስት ስድስት እጥፍ ለሃኪሞቿ ትከፍላለች። የኛ ሀገር ከአለም ለየት ለማለት ነው ሀኪሞቿን በችጋር የምታሰቃየው? ይኸውልህ ይሄ ሙያ እንደሌላው አይደለም። ለአንድ ቀን ቢስተጓጎል ወይ አንተ፣ ወይ ያንተ ከሆኑት አንዱ እስከወዲያኛው ይስተጓጎላሉ።
ቆይ ለምንድነው በየቀኑ ከስንት ታካሚ ጋር፣ በስም ካልሆነ በግብር "የጤና ተቋም" ለማለት በሚከብድ ተቋም ውስጥ ዓመታትን ፈግቶ ሲያበቃ፣ ዛሬም ልጆቹን የሚያበላው፣ የሚያለብሰውና የሚያስተምርበት በማጣት ሲጨንቀው "ደሞዜን አሻሽሉልኝ" ማለቱን እንደ "ጥጋብ" የምታይበት? "ግዴለም እርካታ እየበላህ ኑር" የምትለው አንተ ጠዋት ቁርስህን እርካታ በልተህ ነው የወጣኸው? በባዶ ቤት መኖሩ አንሶ በባዶ ሆዱ ሲያክምህ ነው የሚሻልህ?
አሁን አሁን የሚያሳዝነኝ ደህና ቦታ እንዳይደርሱ፣ ደህና ደህና ጭንቅላት ያላቸውን በሙሉ ነጥቀን ነው ህክምና ት/ት ቤት መክተታችን ነው። ሁለተኛ ጥፋት ደግሞ፣ ሰው እንደተረፈው ሰው ከዚያ አውጥተን ልጆቻችንን እናንገላታለን።
የነዚህ ሰዎች ጥያቄ ፍትሃዊ ነው። መንግስትም ጥያቄውን ሌሎች ለፖለቲካ ፍጆታ እንዳይጠቀሙበት ከፈራ መፍትሄው ጥያቄውን ማፈን ሳይሆን በጊዜ መፍትሄ መስጠት ነው። እነሱም መንግስትን ጊዜ ሰጥተው "በኛ ጉዳይ ተነጋገሩበት፣ አንድ መድትሄ ፍጠሩልን" አሉ እንጂ ዛሬም ስራቸውን እየሰሩ ነው። ሌላ ሃገር ቢሆን ይሄኔ ማጣፊያው አጥሮ ነበር። ጠያቂዎችን ወስዶ እስር ቤት ማጎር፣ የፖለቲካ ታፔላ እየለጠፉ ማሸማቀቅ፣ ማንገላታትና ማባረር ነገ መውደቂያን ይወልዳል። ከማንጓጠጥና ከማጠልሸት ውጪ በአክብሮት መልስ ለመስጠት የሚሞክር እንዴት አንድ ሹመኛ ይጠፋል? እኛ ሀገር ደግሞ ሰው ካልሞተና ህዝብ በጅምላ ካልተቆጣ በስተቀር መፍትሄ አለመስጠት ... ቢያንስ... በዚህ ዙር ቢቀር ጥሩ አይመስላችሁም?
✍️Mitiku Kebede Kayamo, Economist at Indiana University, USA , Researcher, Advisor and MWF Alumni