08/04/2026
በኢራን ህዝብ ቀናሁ።
ኢራናውያን የሚያኮሩ ህዝቦች ናቸው። ዶናልድ ትራምፕ “ኢራንን ወደአመድነት እቀይራለሁ፣ መሰረተ ልማቶች አይተርፉኝም ፣ ሁሉንም አወድማለሁ” ሲል የኢራን ህዝብ ግልብጥ ብሎ ወጥቶ በየባቡር መንገዱና በየኢነርጂ ተቋማቱ እረዥም ሰንሰለት በመስራትና የኢራንን ባንዲራ ይወድማሉ በተባሉ መሰረተ ልማቶች ላይ በማንጠፍ ከሐገራቸው ጎን ቆሙ! እኛንም አብረህ ታወድመናለህ እንጂ ሐገራችንን አናስነካም ነው መልእክቱ።
ኢራናውያን ከሐገራቸው መንግስት ጋር ትልቅ ቅራኔ አላቸው። ያለፈው አመት ለምሳሌ ከፍተኛ ህዝባዊ ቁጣ ተቀስቅሶ ብዙ ሰዎች በሐገሪቱ መንግስት ጉዳት እንደደረሰባቸው ይታወቃል። ነገር ግን የኢራን ህዝብ መንግስትንና ሐገርን ለይቶ የሚያይ የረዥም አመት ያልተቆራረጠ ስልጣኔ ያለው ታላቅ ህዝብ ነውና መቼ ከሐገሩ መንግስት ጎን መቆም እንዳለበትና መቼ ተቃውሞውን ማሰማት እንዳለበት ያውቃል።
እንዳለመታደል ሆኖ እኛ ለዚህ አልታደልንም። የባንዳው ቁጥር መጠን የለውም። ግብፅ ልትወጋን ብትመጣ በዘር ጥላቻ ታውሮና ለጥቂት ፍራንክ ብሎ ሐገሩን ለመሸጥ የተዘጋጀ ብዙ ባንዳና ሹምባሽ ይሰለፋል። ተማርን የሚለውም በየሐገሩ ተበትኖ ሚለፈልፈው ፖለቲከኛ ነኝ ባይ 90 በመቶው የገዛ ሐገሩ ጠላት ሲሆን፣ የሱ የጥላቻ ውቃቢ ይጥገብለት እንጂ ሐገሩ በአንዲት ጀምበር ተበታትና ብታድር ደንታው አይደለም። ይሄ የሚያሳዝን ነገር ግን ልንጋፈጠው የሚገባ የኛ እውነት ነው።
ደግነቱ የባንዳውን ያህል ብዙ አርበኛም አለ። ፖለቲካና ሐገርን ለይተው የሚመለከቱ ጥቂት ምሁራንም አይጠፉም። ባንዳና ሐገር ሻጩ ምን ብዙ ቢሆን ከሐገሩ ጋር የሚሰለፈው ንፁህ ኢትዮጵያዊ ልክ እንደትናንቱ ያሸንፋል።
በኢራን ህዝብ ግን ቀናሁ። ሐገርን ካፈቀሩ ከነ እንከኗ ነው።