27/05/2025
የዝንጀሮ ፈንጣጣ (Mpox) ምንድነው?
=======================
የዝንጀሮ ፈንጣጣ የሚከሰተው ከእንስሳ ወደ ሰው በሚተላለፍ ቫይረሰ አማካኝነት ነው ተብሎ የሚታሰብ ህመም ሲሆን በአብዛኛው ምልክቶቹ ከ 30 ዓመታት በፊት ከዓለም ላይ ጠፍቷል ተብሎ ከሚታሰበው የፈንጣጣ ህመም ጋር ተመሳሳይነት አላቸው፡፡
የመጀመሪያው በሰው ላይ የተከሰተው የዝንጀሮ ፈንጣጣ ህመምተኛ የተገኘው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1970 ዓ.ም በዲሞክራቲክ ኮንጎ ነዋሪ በሆነ የ 9 ዓመት ታዳጊ ላይ ሲሆን የዚህ ህመም መከሰቻ ቦታ ነው ተብሎ የሚታሰበው ደግሞ በመካከለኛውና በምዕራብ አፍሪካ የሚገኙ ሀገራት ነው።
ከእነዚህ ሀገራት ውጪ የመጀመሪያው የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝ የተከሰተው ደግሞ በአሜሪካን ሀገር እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2003 ዓ.ም ሲሆን በዚህም ከ 70 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ተጠቂ ነበሩ፡፡
በተጨማሪም በተለያዩ ጊዜያት በእስራኤል ፣ በዩናይትድ ኪንግደም ፣ በሲንጋፖር እና በአሜሪካን ሀገር መሰል ህመሞች ሲከሰቱ ቆይተው ከግንቦት ወር 2022 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በተለያዩ 12 የዓለም የጤና ድርጅት አባል ሀገራት ላይ የዚህ ህመም አምጪ ቫይረስ ምልክቶች መታየት ችለዋል፡፡
አሁን ባለዉ ሁኔታ ደግሞ የዓለም የጤና ድርጅት ይህንን ህመም አለምዓቀፍ ወረርሽኝ እንደሆነ አስታውቋል፡፡
=> መተላለፊያ መንገዶቹ ምን ምን ናቸው?
ይህ ህመም በዋናነት ይተላለፋል ተብሎ የሚታሰበው ከእንስሳት በሚወጣ የሰውነት ፈሳሽ ፣ በሰውነታቸው ላይ ካለ ቁስለት ጋር በሚደረግ ንክኪ ወይንም ደግሞ በእንስሳቱ ንክሻ ወደ ሰው የሚተላለፍ ሲሆን ህመሙ ካለበት ሰው ወደ ጤነኛው ሰው ደግሞ በተዘረዘሩት ምክንያቶች ይተላለፋል፦
~ከመተንፈሻ አካላት በሚወጡ ፈሳሾች
~በህመምተኛው ላይ ከሚወጡ ቁስለቶች ጋር የሚደረግ ንክኪ
~ህመምተኛው የተጠቀመባቸውንና ከሰውነቱ/ከሰውነቱ ቁስለት በሚወጡ ፈሳሾች የተበከሉ ቁሳቁሶች መጠቀም /ንክኪ መፍጠር
=> ምልክቶቹ ምን ምንድናቸው?
-በማንኛውም እድሜ ክልል ውስጥ በሚገኝ ሰው ሰውነት(ቆዳ) ላይ የሚወጣ ሽፍታ
-እራስ ምታት
-ትኩሳት
-በአንገት አካባቢ የሚገኙ እጢዎች መቆጣት/ማበጥ
-የወገብ ህመም
-ድካም ድካም ማለት
=> ህመሙ ይኖርባቸዋል ተብለው የሚታሰቡ እነማን ናቸው?
~ይህ ህመም እንዳለበት ከተረጋገጠ ሰው ጋር የቅርብ ግንኙነት የነበረው
~ይህ በሽታ እንዳለባቸወደተረጋገቱ ሀገራት በ21 ቀናት ውስጥ የጉዞ ታሪክ ያለው/ያላት
~ባለፉት 21 ቀናት ውስጥ 2 እና ከዚያ በላይ ከሆኑ ግለሰቦች ጋር የግብረ ስጋ ግንኙነት የፈጸመ
=>መከላከያ መንገዶቹ ምን ምን ናቸው?
>የእንስሳት ተዋጽኦ የሆኑ ምግቦችን በሚገባ አብስሎ መመገብ
>ምግብ ከመመገብ አስቀድሞ እጅን በውሀና በሳሙና መታጠብ
>የህመሙን ምልክቶች የሚያሳይን ሰው በአስቸኳይ ወደ ህክምና ተቋም መውሰድ
>ጥናቶች እንደሚያሳዩ ቀድሞ ለፈንጣጣ ይሰጥ የነበረው ክትባት ይህን ህመም ለመከላከል ያስችላል
ያስታውሱ ፦ ይህ ህመም በቶሎ ከተደረሰበትና ተገቢው ህክምና ከተደረገ በቀላሉና በቶሎ የሚድን ነው!