08/02/2022
በሸኔ መንገድ እየሄደን ሸኔን አናሸንፈውም። ጠላት በመረጠልህ መንገድ ከተጓዝክ ተሸናፊ እንጅ አሸናፊ አትሆንም። አሸናፊ ለመሆን ካሰብክ የራስህን መንገድ ቀይሰህ በዚያ መንገድ ብቻ መጓዝ አለብህ። የኦነግ ሸኔና የህወሃት መንገድ የልዩነትና የሞት መንገድ ነው። ከዚህ ውጭ ሌላ ትርጉም ሊሰጠው አይችልም።
የሸኔና የህወሃት ስትራቴጄ ሁለቱን ብሄሮች አጋጭቶ፣ ቢቻል ስልጣንን መቆጣጠር ባይቻል ደግሞ አገርን ማፍረስ ነው። ለምን? አማራና ኦሮሞ አንድ ሆነው፣ ሌሎችን በዙሪያቸው ካሰባሰቡ፣ እንኳንስ ህወሃት፣ የትኛው ሃይል ሊያሸንፋቸው እንደማይችል ይታወቃል። በተግባርም ታይቷል። ስልጣን ለመያዝም ሆነ ኢትዮጵያውን ለማፍረስ፣ አቋራጩ መንገድ እነዚህን ሁለት ብሄሮች ማጋጨት ነው። እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ፣ ለመብት እንቆማለን የምንል ሰዎች፣ ሸኔና ህወሃት በቀደዱልን ቦይ እየፈሰስን፣ ለእነሱ አላማ በተደጋጋሚ ተመቻችተን ስንገኝ እንታያለን። አንዳንድ ጊዜ ያስተውላሉ የምንላቸው ሰዎች ሳይቀሩ፣ በተቀደደላቸው ቦይ እየፈሰሱ፣ ራሳቸውን ተከታዮቻቸውን ለእነዚህ ሃይሎች አመቻችተው ሲሰጡ እናያለን።
ኦነግ ሸኔ በኦሮምያ ክልል፣ አጀንዳውን ከሚደግፉት ባለስልጣናት ጋር ሆኖ፣ የአማራና የኦሮሞ ተውላጆችን ይገድላል። እኛ ደግሞ መርጠን እያለቀስን ገዳዮቹ የሚፈልጉትን ነገር እናደርጋለን። አማራው ሲገደል፣ ኦሮሞው፤ ኦሮሞው ሲገደል አማራው ካላወገዘ፣ የህወሃትና የሸኔ አጀንዳ እየሰራ ነው ማለት ነው። ይህ ግን ከሸኔ ግድያ ጋር ብቻ ተያይዞ የሚታይ አይደለም። ለምሳሌ ባለፈው ሰሞን USAID ለኦሮምያ ክልል ኢንቨርስትመንት 11 ቢሊዮን ብር መደበ ተብሎ፣ የተማረ የሚባለው ሳይቀር፣ "የተረኝነት ማሳያ" እያለ ጻፈ። USAID ቀጠለና ለአማራ ክልል ኢንቨስትመንት 11 ቢሊዮን ብር መድቤያለሁ አለ። ያ "ተረኝነት" እያለ ሲጽፍ የነበረው ሰው ግን ድምጹን አጠፋ። ጎደሎ ሚዛን ማለት ይህ ነው። የብሄርተኝነት ሚዛኑ ጎደሎ ነው የሚባለውም ለዚህ ነው። እነ ሸኔና ህወሃት በሚቀዱት ቦይ መፍሰስ ማለትም ይህ ነው።
የሸኔን ጥቃት ለመቋቋም፣ በተለይ የጥቃቱ ሰለባ የሆኑት አማራና ኦሮሞ፣ በአንድነት ሊቆሙ ይገባል። እርስ በርስ እየተጠራጠሩና እየተወቃቀሱ መሄዳቸውን ማቆም አለባቸው። መንግስትም ውስጡን ተመልክቶ፣ ሁኔታዎች እንዲስተካከሉ የማድረግ ስራ መስራት አለበት። በተለይ ደጋግሞ በተደጋጋሚ ተፈትኖ ዝቅተኛ ውጤት በሚያገኝበት፣ የዜጎችን ደህንነት በማስጠበቅ ስራው ላይ፣ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይኖርበታል። የአንድ አማራ፣ የአንድ ኦሮሞ፣ የአንድ አፋር ወዘተ ደም እንቅልፍ ሊነሳው ይገባል። የአማራና የኦሮሞ ሊህቃን እና የሁለቱ ብሄሮች ህዝብ አንድነቱ እንዲጠናከር፣ ተደጋጋሚ የሊህቃንና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ስራ መስራት አለበት። በእይታ ደረጃም ቢሆን ጥርጣሬ የሚፈጥሩትን ነገሮች ተከታትሎ እርምጃ በመውሰድ ማስተካከል አለበት።
ኢትዮጵያን የሚወዱና የዜጎችን እኩልነት የሚፈልጉ ሁሉ፣ በሸኔና በህወሃት መንገድ እየተጓዙ፣ ህዝባቸውን ማዳን እንደማይችሉ ማወቅ አለባቸው። የስልጣን ምኞት ቢኖራቸውም፣ በዚህ መንገድ ስልጣን መያዝ እንደማይቻል ማወቅ አለባቸው። የእነዚህ ብሄሮች መጣላት ኢትዮጵያን ከማፍረስ ውጭ፣ ሌላ ጥቅም አያመጣም። በፈረሰ አገር ላይ ደግሞ እንኳንስ ስልጣን መያዝ፣ ህይወትንም ማቆየት ፈተና ይሆናል።
የሸኔንና የህወሃትን ጥፋት ማክሸፍ የሚቻለው፣ በልዩነት ሳይሆን እንደ ህዝብ አንድ በመሆን ብቻ ነው ነው።
ፋሲል የኔአለም