24/01/2026
በፈረንሳይ ኔስሊ የተሰኘውን የህፃናት ወተት የተጠቀሙ ሁለት ህፃናት መሞታቸው ተዘገበ።
ከሳምንታት በፊት ኔስሊ ከመርዛማ ኬሚካል ጋር ተነካክተዋል ያላቸውን ምርቶች አሳውቆ ከገበያ እንዲሰበሰቡ ማዘዙ ይታወሳል።
በፈረንሳይ የድርጅቱን ወተት ተጠቅመዋል የተባሉ ሁለት ህፃናት ሞቱ ከተባለ በኋላም ፈረንሳይ ምርመራ ጀምራለች።
አንደኛው የሞተው ህፃን ገና ከተወለደ 2 ሳምንት የሆነው ሲሆን፣ የቦርዶ ከተማ ነዋሪው ልጅ የሞተው ከገበያ እንዲሰበሰብ ከተነገረው ምርት ወተት ከጠጣ በኋላ መሆኑን የልጁ እናት እና መርማሪዎች ገልጸዋል።
ሌላኛው ወተቱን ተጠቅሞ ሞተ የተባለው ልጅ በኦንዠ ከተማ መሆኑ ተነግሯል።
ኔስሊ ፈረንሳይ በጉዳዩ ላይ ለምታደርገው ምርመራ ዝግጁ መሆኑን ገልፆ፣ አሁን ላይ ህፃናቱ የሞቱት በወተቱ ምክንያት እንደሆነ ማስረጃ የለም ብሏል።
የፈረንሳይ የጤና ሚኒስትር እንዲሰበሰብ የታዘዘው ምርት ከገበያ መሰብሰቡን ገልፆ የህፃናቱ ሞት ምርመራ ይደረግበታል ብሏል።
ከኔስሊ በተጨማሪ ከሰሞኑ ላክታሊስ እና ዳኖን የተሰኙ የህፃናት ወተት አምራቾች ምርታቸው ተበክለዋል በሚል ቅድመ ማስጠንቀቂያ ምርቶቹ እንዲሰበሰቡ ጥሪ አድርገዋል።
ዘገባው የፍራንስ24 ነው።
😀 |