15/05/2024
በመድኃኒት ቤቶችና መደብሮች ላይ አስገዳጅ ደረጃ ሊተገበር ነው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2016(ኢዜአ)፦ በሀገር አቀፍ ደረጃ የመድኃኒት ቤቶችና መድኃኒት መደብሮች ላይ አስገዳጅ ደረጃ በቅርቡ ሊተገበር መሆኑን የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ገለጸ።
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የመድኃኒት ቤትና መድኃኒት መደብር ላይ ቁጥጥር ለማድረግ ሀገር አቀፍ አስገዳጅ ደረጃ ወጥቷል።
አስገዳጅ ደረጃው መድኃኒት ቤትም ሆነ መድኃኒት መደብር ምን ዓይነት ባለሙያዎች ሊኖሯቸው ይገባል፣ ምን ዓይነት መድኃኒት ይይዛሉ፣ የመድኃኒት ቤቱ ወይም መደብሩ ስፋት የሚለውንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ያካተተ መሆኑንም ገልጸዋል።
ክልሎች ለመድኃኒት ቤትና መድኃኒት መደብር ፈቃድ የሚሰጡበት መስፈርት የተለያየ መሆኑን አንስተው፤ ወጥነት ያለው ለማድረግ ደረጃው መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
ደረጃው መውጣቱን ተከትሎ አሠራሩ እስኪተገበር ድረስ ለአዲስ መድኃኒት ቤትና መድኃኒት መደብር ፈቃድ እንዳይሰጥ መደረጉንም አንስተዋል።
የባለሥልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር ስዩም ወልዴ በበኩላቸው፤ ከዚህ ቀደም በአገር አቀፍ ደረጃ መድኃኒት ቤቶችና መደብሮች ላይ ደረጃ ወጥቶ ሲሰራ ስላልነበር በክልል ቁጥጥር አካላት ወጥ የሆነ የቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት ሳይቻል ቀርቷል ብለዋል።
ስለሆነም በሁሉም ተቆጣጣሪ አካላት ሊተገበር የሚችል ሀገራዊ መስፈርት ማውጣት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ደረጃው መውጣቱን ገልፀዋል።
በደረጃው የተቀመጡ መስፈርቶች ላይ መመሪያ ተዘጋጅቶ ለክልል ተቆጣጣሪ አካላት ሥልጠና መሰጠቱን ጠቅሰው፤ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።
ደረጃው አዲስ በመሆኑ በወጥነት እንዲተገበር ባለሙያዎችንና ባለድርሻ አካላትን የማሰልጠን ተግባር ይቀጥላል ብለዋል።
https://l.facebook.com/l.php?u=https%3A%2F%2Fwww.youtube.com%2Fwatch%3Fv%3DC2Cwyr6eaPE%26fbclid%3DIwZXh0bgNhZW0CMTAAAR1c-oj2KLdV4ijTprOHhy2em-EU1D4t5_EMahlsS_Ss3q3fY7zcXgfgwMI_aem_AcfUA2T5_sibU0DgVY2ktRt3rL07aYdJ5_KLrjz2RXHUB7ki8ZK564ix_ObqBYj4wg-pGxJMfF71qGgsMcVAFiPf&h=AT1V8u45FB9Amf8qFSSAUW5YIsH_f8aUb1qTqbip11PQAj6yS9-FALs4Qr5zZl2k0PjyjyuqImh0AP_jB5NMy2lmnxoR3GHQrzADlLVOJ69wF_9d86RG8BNq36HDcP_E69r6&__tn__=-UK-R&c[0]=AT2YDjQBWcuALUfnSVCWnilzcLPgG9PEnNJtsyvmFeYOUPXj4KZHvOn5SgR7vfxzO-TJujQjRP6LQtBk8oE27WqiIkE9xVE7EAwSzhA7k8jdoT38M4sMoxeg49aUop4WiXxaldUtmrIQB9HR8y9QeRqkxXtlk5ALtdL_HuDRRsMvSmhmgMNO3l34ODC7FtcpW92Iz-gIblfN3LSLM2pl0t9O7xnl7vajfSoW
#ኢዜአ