22/12/2022
የሚጥል በሽታ(Epilepsy)
የሚጥል ህመም ማዕከላዊ የነርቭ ስርአታችንን በመረበሽ የጭንቅላታችንን አሰራር የሚያውክ ህመም ነው፡፡
አንድ ሰው በአንድ ቀን ውስጥ ሁለት እና ከዚያ በላይ የሆኑ ምክንያታቸው ያልታወቀ መንቀጥቀጦች ካጋጠሙት በሚጥል በሽታ ተጠቅቷል ማለት እንችላለን፡፡
እ.ኤ.አ በ 2019 በወጣው የአለም ጤና ድርጅት ሪፓርት መሰረት በአለማችን ውስጥ 50 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች የሚጥል በሽታ ተጠቂዎች ናቸው፡፡
የሚጥል በሽታ አምጪ ምክንያቶች በትክክል ባይታወቁም በህፃኑ ላይ በወሊድ ጊዜ የሚፈጠር የኦክስጅን እጥረት፤ከዘረመል ጋር የተያያዙ ምክንያቶች፤ኦቲዝም፤ ስትሮክ፤ የጭንቅላት ዕጢ፤ጭንቅላት ላይ የደረሰ አደጋ፤ የጭንቅላት ኢንፌክሽን እንዲሁም ሌሎች ህመሞች አጋላጭ ሁኔታዎች እንደሆኑ ይታመናል፡፡
የሚጥል በሽታ ምልክቶች እንደ አይነቱ ሲለያዩ ለተወሰነ ጊዜ የሚቆይ የሰውነት መንቀጥቀጥ፤ መፍዘዝ፤ የባህሪይ መቀየር፤ራስን መሳት፤ የአይን መገለባበጥ ፤ሰገራን እና ሽንትን አለመቆጣጠር የተወሰኑት ናቸው፡፡
የሚጥል ህመምን ለመመርመር የደም ምርመራዎች፤ኤሌክትሮኢንሴፋሎግራም(EEG)፤ ሲቲ ስካን እና ኤም አር አይ ሊሰሩ ይችላሉ፡፡
የሚጥል ህመም በሀኪም በሚታዘዙ የሚዋጡ መድሀኒቶች ሊታከም ይችላል፡፡ መድሀኒቶቹም ለረጅም ጊዜ ወይም ለእድሜ ልክ ሊወሰዱ ይችላል፡፡ የሚጥል ህመም መድሀኒትን ያለ ሀኪም ፈቃድ ማቆም ህመሙን አባብሶ ለሞት ሊዳርግ ይችላል፡፡
የሚጥል ህመም ያለበት ሰው ድንገት እየተንቀጠቀጠ ስናገኘው በመሸሽ ፋንታ የሚከተሉትን ነገሮች ልናደርግ ይገባል፡-
መንቀጥቀጡ የጀመረበት እና ያቆመበትን ሰአት መመዝገብ እንዲሁም ህመምተኛው ሲንቀጠቀጥ በቪድዮ መቅረፅ ( እነዚህን ማድረግ ሰውየው ያለውን የሚጥል ህመም አይነት ለማወቅ ይረዳናል)
ህመምተኛውን በግራ ጎኑ ማስተኛት
ህመምተኛውን ሊጎዱት የሚችሉትን ነገሮች ከአጠገቡ ማራቅ
የህመምተኛው ጭንቅላት እንዳይጎዳ ከጭንቅላቱ ስር ትራስ ማድረግ
ህመምተኛው እየተንቀጠቀጠ እያለ ምግብ ወይም መጠጥ አለመስጠት
ህመምተኛውን አለማሰር
ህመምተኛው ሲነቃ ከመንቀጥቀጡ በፊት ስለነበረው ሁኔታ ማስረዳት
ህመምተኛውን ወደ ሆስፒታል መውሰድ
የሚጥል ህመም ያለባቸውን ወገኖቻችንን አናግልል!