
29/07/2025
በከሚሴ ጠቅላላ ሆስፒታል ከ1ሺ በላይ ለሚጠጉ የህብረተሰብ ክፍሎች የአይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና አገልግሎት እየተሰጠ ነው።
***
በአማራ ክልል በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ጤና መምሪያ እና የከሚሴ ጠቅላላ ሆስፒታል ከቤተ አብርሃም ክሊኒክ ጋር በጋራ በመሆን የአይን ሞራ ግርዶሽ የቀዶ ህክምና አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
በከሚሴ ጠቅላላ ሆስፒታል ህክምና ሲያደርጉ ካገኘናቸው ታካሚዎች መካከል ወ/ሪት ዘሀራ መሀመድ የቃሉ ወረዳ ነዋሪ ስትሆን ከ12 አመት በላይ የአይን ብርሃኗ እንደማያይ ትናገራለች በዚህም የስነ ልቦና ችግር እንደደረሰባት ገልፃ በተደረገላት የአይን ቀዶ ህክምና የአይን ብርሃኗ ማየት በመቻሏ አዲስ ሂወትን አዲስ መወለድን እና አዲስ ብርሃንን ያየሁበት ቀን ነው ትላለች በዚህም በተደረገላት ህክምና መደሰቷንም ተናግራለች።
ሌሎች በሆስፒታሉ ነፃ የአይን ቀዶ ህክምና የተደረገላቸው ታካሚዎችም በተደረገላቸው ህክምና የአይን ብርሃናቸው እንደተመለሰላቸው ገልፀው በተደረገላቸው ህክምናም አመስግነዋል።
የከሚሴ ከተማ ጠቅላላ ሆስፒታል ስራአስኪያጅ አቶ ካሊድ ሙስጠፋ እንደተናገሩት ከዞን ጤና መምሪያና ረጅ ድርጅቶች ጋር በመሆን ከዚህ በፊት ማየት የማይችሉና እቤት የቀሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመለየት አገልግሎት መስጠት መቻላቸውን ገልፀው ከ1ሺ በላይ የአይን ሞራ ግርዶሽ ያለባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ለመስራት ህክምና እየተደረገ እንደሚገኝም ገልፀዋል።
በቀን ከ150 ሰዎች በላይ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኝ የገለፁት ስራ አስኬጁ የተለያዩ ረጅ ድርጅቶች ጋር በመሆን ቀጣይነት እንዲኖረው ይሰራልም ነው ያሉት።
የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ጤና መምሪያ ተላላፊ በሽታዎችና መቆጣጠር ባለሙያ ወ/ሮ ነፊሳ አብዱ በበኩላቸው ከዞን ጤና ከከሚሴ ጠቅላላ ሆስፒታልና ከቤተ አብርሃም የአይን ክሊኒክ ጋር በጋራ በመሆን ለ6ኛ ጊዜ የአይን ብርሃን ግርዶሽ ያለባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች የአይን ብርሃናቸውን ለመመለስ ሰፊ ስራ ሲሰራ መቆየቱን ገልፀው 1200 የሚጠጉ ከተለያዩ አጎራባች ወረዳዎች የህብረተሰብ ክፍሎችን አገልግሎት እንደሚሰጥም ገልፀዋል።
የአውትሪቹ ኮርዲኔተር ሲስተር መሰረት ፋንታሁን እንደተናገሩት ቤተአብርሃም ክሊኒክ ከዞን ጤናና ከከሚሴ ጠቅላላ ሆስፒታል ጋር በመሆን የአይን ሞራ ግርዶሽ ላለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ገልፀው ህብረተሰቡን ተደራሽ ለማድረግ ቀጣይነት እንዲኖረው ይሰራል ብለዋል በዚህም ለታካሚዎች ክትትል እንደሚደረግም ተናግረዋል።