08/10/2025
መቃብር ቦታ ያልጠበቁትን ነገር ተመለከትኩ!!
እረፍት ሳገኝ አንዳንዴ ወደ መቃብር ስፍራ መሄድ ያስደስተኛል።ከራስ ጋር ጊዜ ለማሣለፍ፣የጠፋውን እና በግርግር ጭልጥ ያለው ማንነታችን ለመፈለግ እና ለማግኘት ቆንጆ ስፍራ ነው።
ሰው ሟች እንደሆነ ከተራዳ የህይወት ፍጻሜውን አውቋልና ለመኖር አይከብደውም።
አንድ ቀን ግን መቃብር ቦታ ያልጠበቁትን ነገር ተመለከትኩ፤ ያየሁት የመቃብር ላይ ፅሁፍ ስላስገረመኝ ይሄን ሰው በደንብ ማወቅ አለብኝ አልኩና ስሙን ይዤ ማህበራዊ ሚድያ ላይ መፈለግ ጀመርኩ ።
የህክምና ባለሙያ እንደሆነና በካንሰር በሽታ ለብዙ ወራቶች ተሰቃይቶ በ 30 ዓመቱ እንዳረፈ መረጃ አገኘሁ
መቃብሩ ላይ የተፃፈው እንዲህ ይላል "የእኔም ተራ ደረሰና መጣሁ"
የተራ ጉዳይ እንጂ ሁላችንም ሞትን ቀማሽ ነን።ነገር ግን በብዙ የህይወት ውጣ ውረድ ስንዳክር ሞት እንዳለ ረስተን ድንገት ይመጣና ይዞን ላይመለስ ይሄዳል::
እዚህ ዓለም ላይ እየኖርን ሳይሆን እያለፍን ነው ፤ የምንሞተው መሞታችንን በምንረሳበት ቅጽበት ነው፤ እንድንሞት የሚያስታውሱን ነገሮች ሁሉ ህይወት ይሰጡናል።
የግሪክ አካባቢ ሰዎች መሞታቸው የሚያስታውሳቸውን ነገር በኪሳቸው ይዘው ይንቀሳቀሳሉ። "ሜሜንቶ ሞሪ " የሚል ቃል አላቸው ትርጓሜውም 'አስታውስ ትሞታለህ' የሚል ነው። ይሄን ፅሁፍ ሲመለከቱ ክፋት ያሰበ ከክፍቱ ይቆጠባል፤ ምቀኛው ፣ ዘራፊው፣ ነፍሰ ገዳዩ ከድርጊታቸው ይታቀባሉ።
ለዛም ነው በታላቁ መፅሐፍ "ወደ ግብዣ ቤት ከመሄድ ወደ ልቅሶ ቤት መሄድ ይሻላል፤ እርሱ የሰው ሁሉ ፍጻሜ ነውና፥ ሕያውም የሆነ በልቡ ያኖረዋልና" (መክ 7:2) ይለናል።
መሞታችንን ስናውቅ መኖር እንጀምራለን።
ተጻፈ በዶ/ር ኃይለልዑል መኮንን (ነሀሴ 1/2017 ዓ.ም)