
09/26/2021
ህይወት ተገላቢጦሽና ኮሜዲ ናት ....
አንደኛው ...የዩክሬን ህዝብ ከአንድ አመት በፊት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው የሀገሪቱን ትልቅ ሀላፍትና ለአንድ ግለሰብ ይሰጣሉ። ግለሰቡ ከጥቂት አመታት በፊት ይሰራ የነበረው ስራ ኮሜዲያንነት ነበር።
አዎ በመድረክ ላይ ቀርቦ የተሰበሰቡትን ሰዎች ቀልድ እየፈጠረ ማሳቅ ነበር ስራው። በዛ ላይ ዩክሬይንና ከታላቋ ራሺያ ጋር በመሬት ዙሪያ ከፍተኛ ወታደራዊ ፍጥጫ ውስጥ በገባችበት ወቅት ነበር የሀገሪቷን ከፍተኛ ስልጣን የተቆናጠጠው። ዩክሬናዊያን አምነው የሰጡት ስልጣን የሀገሪቱ ፕሬዝዳንትነት ነበር።
ነገር ግን ይላሉ የፖለቲካ ተንታኞች ዘለንስኪ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ከሆነ በኃላ ራሺያ አላግባብ የወሰደችውን የክሬሜሪያ ግዛት እንድትመልስ በዲፕሎማሲያዊም ሆነ በጦርነት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል።
የተቀዛቀዘውን የሀገሪቱን ብሔራዊ ስሜት ለመመለስ ጥረት አድርጓል። ተሳክቶለታልም። የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ አዳዲስ ፖሊሲዎችን ተተግብሮአል። በእራሱ ጥረት የኔቶን የጦር እርዳታ ለማግኘም ችሏል።
ፕሬዚዳንት ከሆነ ሁለት አመት አልሆነውም ነገር ግን ለሀገሩ ብዙ ስራዎችን ሰርቷል። በዚህም ከስልጣን በፊት ኮሜዲያን ከስልጣን በኃላ ትክክለኛ መሪ ለመሆን በቅቷል።
ሁለተኛው ...በወታደራዊ ህይወት አልፏል። በህይወቱ የተለያዩ ውጣ ውረዶችን አሳልፌያለሁ ይላል። ከሰባት አመቱ ጀምሮ የሀገር መሪን ስለመሆን እያሰበ እንዳደገ ይናገራል። በትምህርትም ዶክትሬት ደረጃ ደርሻለሁ ብሎ ተናግሯል።
እሱ ስልጣን ሲይዝ ህዝቡ ትክክለኛ መሪ እንዳገኘ ተማምኖ ነበር። ንግግሮቹ ግሩም ነበሩ። የታላቁ ሙሴ የአሻጋሪነት ታሪክ ሊደገም ነው ያሉም ብዙሃን ነበሩ። እሱ ስልጣን ከያዘ በኃላ ግን የጠበቅነው ሳይሆን ያልጠበቅነው ሆነ።
መሪ ብለን ያሰብነው ግለሰብ ኮሜዲያን ሆኖ አረፈው። የሀገሪቱን ችግር ከመፍታት ይልቅ በየትያትር ቤቶች የሚያሳልፍ ሆኖ ተገኘ። በተግባር ከመስራት ይልቅ የወሬ ንጉስ ሆኖ ተከሰተ። ችግሮችን በብስለት ከመምራት ይልቅ እንደ አፍላ ወጣት በስሜት የሚወስን ሆኖ አገኘነው።
ታሪክ ይሰራል ብለን ስንጠብቅ ቀኑን ሙሉ ፎቶ እየተነሳ ታሪክ ሰርቶ አረፈው። ሰላም ያመጣል ብለን ጠብቀን ጦርነት አቀጣጣይ ሆኖ አረፈው። የህዝብ ደህንነት ይጠብቃል ብለን ጠብቀን ገዳይ ሆኖ አረፈው።
ያታርቃል ብለን የሚያጣላ .. ያሻግራል ስንል ገደል የሚገባ .. ሀገር ይመራል ብለን ቤተመንግስቱን የሚያድስ ... ጠቅላይ ሚኒስትር ተመኝተን ንጉስ .. ያስከብረናል ብለን ያስናቀን ... ያጠናክረናል ብለን ያዳከመን ...ወዘተ ወዘተ ...የሆነ ኮሜዲያን አግኝተን አረፍነው።
ህይወት እንግዲህ እንዲህ ናት !!!
Finfinne Times ፊንፊነ ታይምስ