
07/02/2023
ሶሻል ፎቢያ (Social phobia)
---------------------------------------
ሶሻል ፎቢያ ያለባቸው ሰዎች ሌሎች ሰዎች ባሉበት ዘና ማለት አይችሉም፡፡ ሌሎች ሰዎች የእነሱን ንግግር ወይም ድርጊት የሚገመግሙና የሚተቹ ስለሚመስላቸው ይፈራሉ፡፡ስህተት እንዳይሰሩና እንዳይዋረዱ ስለሚፈሩ ዘና ብለው እንደሚፈልጉት ከሰዎች ጋር መጫወት ይከብዳቸዋል ፡፡
አብዛኛው ሰው ካልለመደው ሰው ጋር ሲሆን የአለመመቸት ስሜት ይፈጠርበታል፡፡ ሶሻል ፍቢያ ሲሆን ግን ፍርሀቱ በጣም የበዛ ይሆናል፡፡ ሶሻል ፎቢያ ያለባቸው ሰዎች አብሯቸው ያሉ ሰዎች ሲጫወቱ ፣ሲስቁ ፣ሲያወሩ እነሱ መሣተፍ ስለማይችሉ ብቸኝነት ይሰማቸዋል፡፡
ብቻቸውን ግን አይደሉም፡፡ ከአስር ሰው አንዱ ተመሣሣይ ሁኔታ ውስጥ ነው፡፡ ነገ መንገድ ላይ ሲሄዱ አስር ሰዎች ይቁጠሩ ከዛ ውስጥ አንዱ ሶሻል ፍቢያ አለበት/አለባት፡፡
የሶሻል ፎቢያ ምልክቶች በጥቅቱ፦
-ከቤት ውጪ ምግብ ባይበሉ ይመርጣሉ፡፡ለብቻቸው ሬስቶራንት ገብተው፣ ባዶ ጠረጴዛ ፈልገው፣ 'ያ ሁሉ ሰው' እያያቸው መመገብ ይከብዳቸዋል፡፡
-ዝግጅቶች ላይ በግድ ነው የሚገኙት (እሱንም ከተገኙ!)-እስከቻሉት ድረስ ምክኒያት ፈጥረው ለመቅረት ይሞክራሉ፡፡
-በአብዛኛው የድካም ስሜት ይሰማቸዋል፡፡
-ሰዎች ሲሰበሰቡ ከመጨነቅ ጋር ተያይዞ ልብ ቶሎ ቶሎ መምታት፣ ትንፋሽ ቁርጥ-ቁርጥ ማለት፣ ማላብ
- ነገሮች እጅግ አስከፊ ሊሆኑ እንደሚችሉ በማሰብ መጨናነቅ ፣እንቅልፍ ማጣት
- የፍቅር ቀጠሮች ላይ (በተለይ የመጀመሪያዎቹ ላይ) ምን እንደሚባል አለማወቅ...
ከላይ የተዘረዘሩትን ሶሻል ፎቢያ ያለባቸው ሰዎች ይረዱታል፡፡ ሌሎች ግን ቀለል አድርገው ሊያዩት ይችላሉ፡፡ ሶሻል ፎቢያ ተማሪዎች እውቀት እያላቸው ጥሩ ውጤት እንዳይኖራቸው፤ ሰራተኞች ችሎታ እያላቸው የሚገባቸውን እድገት እንዳያገኙ፣ እንዲሁም ለሚወዱት ሰው ፍቅራቸውን መግለፅ እንዳይችሉ ያደረጋል፡፡
ሶሻል ፎቢያን ማሸነፍ ይቻላል ነገር ግን ትዕግስትና ቁርጥኝነት ይጠይቃል፡፡
በራሳችን ልናደረግ የምንችለው
1. ሀሣብን መገምገም፦ በሶሻል ፎቢያ የሚቸገሩ ሰዎች ጭንቀትን የሚያባብሱ ሀሳቦች አላቸው፡፡
ለምሳሌ ፡- ፡"እንደ ሞኝ መቆጠሬ አይቀርም፡፡" "መናገር ስጀምር ድምፄ ይንቀጠቀጥና ራሴን አዋርዳለሁ፡፡ " "አንደፈራሁ ሰዎች ያውቁብኛል፡፡" እነዚህን ሀሣቦች መገመገምና መሞገት ጭንቀቱን ይቀንሣል፡፡
2. ከሰዎች ጋር ሲሰበሰቡ ሌሎች ላይ ማተኮር፤ በራስ ጭንቀት ከመጠመድና ፍርሃትን ስለመሸፈን ከመጨነቅ ሌሎች ሰዎች የሚያደርጉትና የሚናገሩት ነገር ላይ ማተኮር ጭንቀትን ይቀንሳል ፡፡ ሰዎች በአብዘኛው የሚያስቡት ስለራሳቸው ስለሆነ የሚገምተውን ያህል መፍራታችንም አያውቁም፡፡
3. አተነፋፈስን ማስተካከል - በፍርሃት ጊዜ በአብዛኛው ከላይ-ከላይና ቶሎ-ቶሎ ነው የሚተነፈሰው ፡፡ ይህ ጭንቀትን ያባብሳል ፡፡- በቀስታ በጥልቀት መተንፈስ ረጋ ያለ ስሜትን ይፈጥራል ፡፡
4. አነቃቂ ነገሮች የጭንቀት ስሜትን ስለሚያባብሱ እነሱን መቀነስ፡፡
እነዚህ ተደረገው አሁንም ስሜቱ ካለ የህክምና እርዳታ ያስፈልገዋል፡፡
ያለ አእምሮ ጤና፤ ጤና የለም!!!
ዶ/ር ዮናስ ላቀው