
26/05/2024
#ስኳር ያለባቸው ነፍሰ ጡር እናቶች ኢንሱሊንን ሆድ ላይ መወጋት ይችላሉን?
አብዛኛዎቹ ነፍሰ ጡር እናቶች ኢንሱሊን ሆድ ላይ ለመወጋት ይፈራሉ፣ መርፌው ጽንሱን ይጎዳዋል ብለው ይጨነቃሉ። የስኳር ህመም ላለባቸው ነፍሰ ጡር እናቶች ኢንሱሊን ለመውጋት ተመራጩ ቦታ ሆድ ነው። በእርግዝና ወቅት ኢንሱሊንን ሆድ ላይ መውጋት ደህንነቱ የተጠበቀ ነው። ሆድ ኢንሱሊንን ለመውሰድ ቀላልና አመቺ ቦታ ብቻ ሳይሆን ኢንሱሊን ወደ ሰውነት በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲገባ (predictable insulin absorption rate) ስለሚረዳ ለኢንሱሊን አወሳሰድ የሚመከር ቦታ ነው። የኢንሱሊን መርፌው ለጽንሱ ምንም አይነት ስጋት አይፈጥርም ምክንያቱም ማህፀኑ ጽንሱን በበቂ ሁኔታ ከለላ ይሰጠዋል። ስለዚህ, የመጀመሪያ ጥያቄያችንን ለመመለስ, አዎ, በእርግዝና ወቅት ኢንሱሊን ሆድ ላይ መውጋት በአጠቃላይ ደህንነቱ የተጠበቀ ነው።
በእርግዝና ወቅት ኢንሱሊንን ሆድ ላይ መውጋት ደህንነት ካረጋገጥን በመቀጠል በተለያዩ የእርግዝና ወቅቶች መደረግ ስላለባቸው የተወሰኑ ምክሮችን ስናይ
1. በመጀመሪያው ሶስት ወር የእርግዝና ጊዜ (first trimester) የኢንሱሊን መርፌ በየትኛውም የሰውነት ክፍል ላይ መወጋት ይቻላል:: ከእርግዝና በፊት የነበረ ስኳር ያለባቸውና ኢንሱሊን የሚወስዱ እናቶች የመጀመሪያው ሶስት ወር የኢንሱሊን መውጊያ ቦታ ወይም ቴክኒክ ለውጥ አያስፈልግም።
2. በሁለተኛው ሶስት ወር (second trimester) ጊዜ ሲደርስ የሆድ ገጽታ መለወጥ ይጀምራል፤ ጽንሱ ያድጋል እና ሆድም እንዲሁ። ይሁን እንጂ ኢንሱሊን ሆድ ላይ መውጋት መተው አለብን ማለት አይደለም። ይልቁንስ የመርፌ መወጊያ ቦታን መጠነኛ ማስተካከያ ማድረግ ይችላሉ።በእምብርት ዙሪያ ከጽንሱ ፊት ለፊት ያለውን የሆድ ክፍል ይልቅ ጽንሱ ካለበት በደንብ ራቅ ብለን ከጎን ያሉት የሆድ ክፍሎች ኢንሱሊንን ለመወጋት መጠቀም ይቻላል።
3. በመጨረሻ ሶስተኛው ወር (third trimester) ልጁ እያደገ የመርፌ መወጊያ ቦታ እየጠበበ ይሄዳል እንዲሁም ቆዳ በሆድ ላይ በጣም ጥብቅ ሊል ይችላል። እንዳንዴ ለኢንሱሊን መርፌ መወጊያ የሚሆን ምቹ ቦታ ማግኘት ሊከብድ ይችላል። እንዲህ ሲያጋጥም አይጨነቁ ፣ መፍትሄ አለ ።
መምረጥ ያለብን ቦታ በጎን የሆድ ክፍል ያለውን መሆን አለበት። ቦታውን በአውራ ጣት እና ጠቋሚ ጣት መሀል ቆንጠጥ በማድረግ ቆዳውን ትንሽ በማንሳት መወጋት ይቻላል:: ከሆድ ጋር ጥብቅ ያለውን ሳይሆን በጣቶች መሃከል ላይ ቆዳን ከፍ ማድረግ የሚቻልበት ቦታ በሆድ ጎን ላይ ያግኙ። ከዚያም መርፌውን ከቆዳ በ90 ዲግሪ ቀጥታ አስገብቶ መውጋት ይቻላል።
ይህ ዘዴ ምቹ እና ውጤታማ ሲሆን የኢንሱሊን መርፌን ለመወጋት ተመራጭ መንገድ ነው። ከተገኘ በጣም አጭር የኢንሱሊን መርፌ (በ4 ሚሊ ሜትር) መጠቀም ጥሩ ነው። ይህን የማይመርጡ እና ጽንሱን እንዳልውጋው የሚል ከፍተኛ ፍርሃት ያለባቸው እናቶች እንደአማራጭ ክንድ፣ ታፋ ወይም መቀመጫ ላይ ሊወጉ ይችላሉ።