
24/05/2025
ታላቅ የምስራች ከሂል አፍሪካ ሄልዝ ሲቲ አ.ማ.
የሂል አፍሪካ ሄልዝ ሲቲ አ.ማ. አካል የሆነዉ ቤቴል ቲቺንግ አጠቃላይ ሆስፒታል ከረዥም ግዜ የጥገና ሂደት በኋላ ጥራቱን የጠበቀ የህክምና አገልግሎት መስጠት ጀመረ!
በሀገራችን ፈር ቀዳጅ የሆነዉ ቤቴል ቲቺንግ አጠቃላይ ሆስፒታል በህዳር 1993 በዶ/ር ይገረም አስፋዉ ተመሰርቶ ከ20 አመታት በላይ በምስራቅ አፍሪካ ፋና ወጊ በሚባል ሁኔታ የህክምና አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱ ይታወሳል። በመሆኑም ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት ይሰጥ ዘንድ መሰረታዊ የሆነ የእድሳት እና የግንባታ ሥራ ላይ የነበረዉ ሆስፒታሉ በዛሬዉ እለት ቅዳሜ ግንቦት 16 ቀን 2017 የቦርድ አባላት፣ ከፍተኛ የስራ አመራሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዳዎች በተገኙበት በይፋ ተመርቋል። የመክፈቻዉን ንግግር ያደረጉት የሆስፒታሉ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዶ/ር ሰኢድ መሀመድ እንደገለጹት ቤቴል ቲቺንግ አጠቃላይ ሆስፒታል ላለፉት በርካታ ወራት በእድሳት ስራ ላይ ረዘም ያለ ጊዜ ማሳለፉን ጠቅሰዉ አብዛኛዉ ሰዉ ሲጠይቅ የነበረው መች አልቆ ወደ ስራ ይገባል የሚል ጥያቄ እንደነበረ አስታዉሰዉ ሁላችንም በጉጉት ስንጠብቀዉ ለነበረዉ ቀን እንኳን አደረሰን ሲሉ ደስታቸዉን ገልፀዋል።
በመቀጠልም የሂል አፍሪካ ሄልዝ ሲቲ አ.ማ. ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ጀማል ሰዒድ እንደገለጹት ቤቴል ቲቺንግ አጠቃላይ ሆስፒታል ወደኋላ ዞረን ቀዳሚ፣ መስራች እንዲሁም ፈር ቀዳጅ እያልን ስንገልጸዉ የነበሩውን የህክምና አገልግሎት ወደፊት የምናስቀጥልበት የሽሽግር ቀን ነዉ ሲሉ ገልፀዉታል። በስመጥር የጤና ባለሞያዎች፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ከወረቀት-ነፃ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅቱን መጨረሱንና ሆስፒታሉ ከነገ ማለትም ግንቦት 17 ቀን 2017 ጀምሮ ለታካሚዎች ክፍት መሆኑን አብስረዋል።
ለመላው የሂል አፍሪካ ቤተሰቦች እንኳን ደስ አላችሁ!!