27/03/2026
" የቲቢ መድኃኒት በነፃ ነው፤ ከፍሎ የሚወስድ የተሰረቀ መድኃኒት እየገዛ ነው " - ጤና ሚኒስቴር
በኢትዮጵያ በየአንድ ሰዓቱ የሁለት ሰዎች ሕይወት በቲቢ በሽታ ምክንያት እንደሚቀጠፍና ሀገራችን የበሽታው ከፍተኛ ጫና ካለባቸው 30 የዓለም ሀገራት ውስጥም አንዷ መሆኗ ተገለጸ።
ይህ የተገለጸው የዓለም የቲቢ ቀንን ምክንያት በማድረግ በጤናው ዘርፍና በሚዲያ ባለሙያዎች መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር ጤና ሚኒስቴር ባዘጋጀው የሚዲያ ፎረም ላይ ነው።
በጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ህይወት ሠለሞን እንደገለጹት ፤ መንግሥት ለአንድ የቲቢ ታካሚ በዓመት ከ6 እስከ 8 ሺህ ዶላር ወጪ እያደረገ ይገኛል።
" የቲቢ መድኃኒት ለታማሚዎች በነፃ ነው የሚሰጠው ፤ ከዚህ ውጭ መድኃኒቱን ከፍሎ የሚወስድ ሰው ካለ እየገዛ ያለው የተሰረቀ መድኃኒት ነው " ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
በአሁኑ ወቅት ከ2,000 በላይ የግል ጤና ተቋማት ምርመራና ሕክምና እየሰጡ ሲሆን ለ1,000 ተቋማት መመርመሪያ መሣሪያዎች መሰራጨታቸውን ገልጸዋል። በገጠሩ አካባቢ ለሚገኙ 690 ላቦራቶሪዎች የሶላር ፓነል ዝርጋታ መከናወኑን አመልክተዋል።
በሚኒስቴሩ የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዴስክ ኃላፊ አቶ ታዬ ለታ በበኩላቸው ፥ ባለፉት 6 ወራት ብቻ የሶማሌ ክልልን ሳይጨምር ለ138,000 ሰዎች በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) የታገዘ ምርመራ ተደርጎ 3,500 ያህል የቲቢ ተጠቂዎች መገኘታቸውን ተናግረዋል።
አክለውም ፥ በሀገራችን ከሚከሰቱ የቲቢ አይነቶች 70% ሳምባን የሚያጠቁ ሲሆኑ፣ 30% ደግሞ ሌሎች ሁሉንም የሰውነት ክፍሎችን እንደሚያጠቁ ተናግረዋል።
ምልክቶቹ ፦
• ለሁለት ሳምንትና ከዚያ በላይ የሚቆይ ሳል፣
• ትኩሳት፣
• ማታ ማታ ማላብ፣
• የሰውነት ክብደት መቀነስ፣
• አልፎ አልፎ ደም የቀላቀለ አክታ ናቸው።
አቶ ታዬ በዓለም ላይ በየዓመቱ 10.7 ሚሊዮን ሰዎች በቲቢ እንደሚያዙ ከ1.2 እስከ 1.3 ሚሊዮን የሚደርሱትም ሕይወታቸውን እንደሚያጡ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በዓመት 19,000 ሰዎች ይሞታሉ።
" አንድ የታመመ ሰው ሲያስል ወይም ሲያስነጥስ እስከ 40,000 ሚደርሱ ጥቃቅን ጠብታዎችን ፤ ለ5 ደቂቃ ብቻ ሲያወራ ደግሞ 3,000 ጠብታዎችን ወደ አየር በመልቀቅ በሽታውን በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው ያሰራጫል " ብለዋል።
ሰዎች ሲያስነጥሱ ወይም ሲያስሉ አፍና አፍንጫቸውን በክንድ ወይም ባማስክ መሸፈን አለባቸው ሲሉ አስገንዝበዋል።
በየዓመቱ የብዙ ሰዎችን ህይወት እየቀጠፈ ቢሆንም ብዙ ሰው ግድ አይሰጠውም ብለዋል።
እስካሁን 150,000 ታካሚዎች ወደ ሕክምና ማስገባት ቢቻልም አሁንም 30,000 "የተደበቁ" ታማሚዎችን ለማግኘት የጤና ባለሙያዎች ቤት ለቤት ፍለጋ እያደረጉ እንደሚገኙ አመልክተዋል።
ለቲቢ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑት ፦
- ከታካሚ ጋር የሚኖሩ፣
- ስኳርና ኤችአይቪ ያለባቸው
- የአየር ዝውውር በሌለው ቤት የሚኖሩ ናቸው።
በሌላ መረጃ ፥ ባለፉት 6 ወራት 1,460 አዳዲስ የሥጋ ደዌ ታማሚዎች ተለይተዋል። በአሁኑ ወቅት 1,800 ሰዎች በሕክምና ላይ ናቸው። ይህ ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በዚህ በሽታ በዓመት እስከ 3000 ሰዎች ይሞታሉ።