12/02/2024
ጤና ይስጥልኝ !
ስለ ኢንሱሊን መላመድ (Insulin resistance) ጥቂት እንማማር።
ስለ ኢንሱሊን መላመድ ለመረዳት በቅድሚያ የኢንሱሊንን ምንነት እና አሰራሩን ከመረዳት መጀመር ይጠቅመናል። ኢንሱሊን ሰውነታችን ውስጥ የሚገኝ ሆርሞን ሲሆን የሚመረተውም ጣፊያ በተባለው አካል ውስጥ ነው። ይህ ሆርሞን በሰውነታችን ውስጥ በዋናነት የሚጠቅመን የደም ስኳር (Blood glucose) ትክክለኛ መጠኑን ጠብቆ እንዲቆይ በማድረግ ነው። ምግብ በሰውነታችን ውስጥ አስፈላጊውን ሂደት በማለፍ ወደ የደም ስኳርነት (Blood glucose) ሲቀየር ጣፊያ ኢንሱሊንን ወደ ደማችን እንዲለቅ መልዕክት ይተላለፍለታል። በዚህ ጊዜ ኢንሱሊን በደም ውስጥ ያለውን ስኳር ሴሎቻችን እንደ ሃይል ምንጭ እንዲጠቀሙት ያደርጋል።
ምግብ በማንበላበት ጊዜ ደግሞ በሰውነታችን ውስጥ ያለው የደም ስኳር መቀነስ የኢንሱሊን መጠን እንዲቀንስ ያደርገዋል፤ ይህም በተዘዋዋሪ ጉበታችን ውስጥ ቀደም ሲል የተጠራቀመ የደም ስኳር እንዲለቀቅ ያደርጋል።
ይሄ መደበኛው ሂደት ሲሆን ኢንሱሊን ሬዚስታንስ እንዴት ሊከሰት ይችላል የሚለውን ደግሞ እንመልከት:: በተደጋጋሚ ምግብ በምንበላበት ጊዜ ብዙ ስኳር ወደ ሰውነታችን ስለሚገባ ይህን ለመቆጣጠር ጣፊያ ብዙ ኢንሱሊን እንዲያመነጭ ምልክት ይሰጠዋል፤ ነገር ግን በሂደት ሴሎቻችን ለኢንሱሊን ምላሽ መስጠት የማይችሉበት እና እርምጃ የማይወስዱበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፤ በዚህ ጊዜ ኢንሱሊንን ተላመዱ ወይም insulin resistant ሆኑ እንላለን።
ይህንንም ለማስተካከል ጣፊያ ብዙ ኢንሱሊን ማመንጨቱን ይቀጥላል፣ ኢንሱሊን የደም ስኳሩን በጉበትና ጡንቻ ውስጥ ለማስቀመጥ ምልክት ይሰጣል ፤ እነኚህ ሲሞሉ ጉበት የተቀረውን የደም ስኳር ወደ ስብ (fat cells) በመላክ እንደ ስብ እንዲጠራቀም ያደርጋል። ይህም ለክብደት መጨመር፣ ቅድመ ስኳር ህመም (pre-diabetes) እና የስኳር ህመም ተጋላጭነታችንን ይጨምራል።
እንደ አጠቃላይ አንድ ሰው የኢንሱሊን መላመድ እንዳጋጠመው ለማወቅ የሚደረግ ቀጥተኛ የላብራቶሪ ምርመራ ባይኖርም እነዚህ ምልክቶች ካሉበት ኢንሱሊን ሬዚስታንስ አጋጥሞት ሊሆን እንደሚችል ጠቋሚ ሊሆን ይችላል።
• በተደጋጋሚ ከፍ ያለ እና የማይቀንስ የደም ስኳር መጠን
• ከፍተኛ የደም ቅባት (cholesterol) መጠን
• ከፍተኛ የሆነ የደም ግፊት
• ቆዳ ላይ የሚወጣ ጠቆር ያለ ምልክት (acanthosis nigricans)
• የወገብ ዙሪያ ልኬት (waist circumference) ለሴቶች ከ89 ሳ.ሜ. በላይና ለወንዶች ከ102 ሳ.ሜ. በላይ ከሆነ
• በቤተሰብ ውስጥ የቅርብ ሰው የስኳር ህመም (በተለይም አይነት 2) ካለው
• ከፍተኛ የሆነ የሰውነት ክብደት (በተለይ የወገብ ዙሪያ) ካለ፣
• ብዙ እንቅስቃሴ አለማድረግ፣
• ሰአቱን ያልጠበቀ የአመጋገብ ስርዓት
• ሲጋራ የማጨስ ልምድ
ለኢንሱሊን ሬዚስታንስ ተጋላጭነትን በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል።
ለማስተካከልም
• አካላዊ እንቅስቃሴን ማዘውተር
• የሰውነትን ክብደትን ማስተካከል/ ጤናማ የሰውነት ክብደት እና የስብ ክምችት ብቻ እንዲኖር ማድረግ።
• ጭንቀት ካለ መቀነስ ወይም manage ማድረግ
• በቂ እንቅልፍ ማግኘት።
• ጊዜውን የጠበቀ፣ መጠኑን ያላለፈና የተመጣጠነ የአመጋገብ ስርዓትን ማዘውተር ይኖርብናል።
ስለዚህ ይህንን ለብዙ ሕመሞች የሚያጋልጠውን የጤና ሁኔታ በመከላከል ወይም በመቆጣጠር ጤናዎን እንዲጠብቁ እንመክራለን።
ጤናማ ቆይታ!
ኢማን ዘኪ (ዳይቲሺያን)
References:
1.https://www.niddk.nih.gov/health-information/diabetes/overview/what-is-diabetes/prediabetes-insulin-resistance
2. https://diabetes.org healthy-living medication-treatments/insulin-resistance
3.https://diabetes.org/healthy-living/medication-treatments/insulin-resistance