06/03/2026
ትውልዱ ወዴት እየሄደ ነው?
ከክሊኒኩ በር ላይ የ14 ዓመት ታዳጊ ቆማለች። አይኖቿ ውስጥ ፍርሃት የለም፤ አለባበሷ፣ አነጋገሯ እና በራስ መተማመኗ ከማህበራዊ ሚዲያ አነቃቂዎች የተገኘ እንደሆነ ያስታውቃል።
እናቷ ከበስተጀርባዋ ትከተላለች፤ አይኖቿ በእንባ እና በጭንቀት ደፍርሰዋል። ልጇ በተለያዩ ሱሶች ውስጥ እየዋኘች እንደሆነ ብታውቅም፣ ምን ማድረግ እንዳለባት ግራ ገብቷት ዝምታን መርጣለች። ከፊት ለፊቴ ተቀምጣ አይን አይኔን እያየች እንዲህ አለችኝ፦ "ዶክተር... ለምን ትገረማለህ? ይሄ እኮ ሁሉን ነገር የምሞክርበት እድሜዬ ነው። አዳዲስ ነገሮችን መሞከር ደግሞ ኖርማል ነው!"
"Normal" የሚለው ቃል ትርጉሙ መቼ ተቀየረ? ሱስን መጠቀም፣ አካልን እና አእምሮን በኬሚካል ማደንዘዝ እንደ ስልጣኔ ሲቆጠር መስማት ያስገርማል።
ይህ ትውልድ በክፍት በሮች መካከል እንዳለ ይሰማኛል። መረጃ በጣቶቹ ስር ነው፤ አለም ደግሞ "የፈለከውን ሁን" እያለችው ነው። ለመሆኑ ሙከራ ማለት ጥፋትን መቅመስ ማለት ነውን? ወላጆችስ "ልጄ እንዳይከፋት" በሚል ስም ዝምታን ሲመርጡ ጥልቁን ገደል እያመቻቹ ይሆን? "ይሄ እድሜዬ ነው" ከሚለው በራስ መተማመን በስተጀርባ ያለው ድምፅ የድረሱልኝ ጥሪ ይሆን ወይስ የጥፋት ጩኸት ?
ዝምታ መፍትሄ አይደለም፣ ፍቅር ማለት ሁሉንም ነገር መፍቀድ ማለት አይደለም። ልጆቻችን የመሞከሪያ እድሜ እያሉ ህይወታቸውን ሲያቃጥሉ "ኖርማል ነው" ብለን ከተቀበልን ነገ የምናቅፈው ትውልድ ሳይሆን አመድ ይሆናል።
ልጅን መውደድ ማለት የሚሰሩትን ስህተቶች ዝም ብሎ ማየት አይደለም። ዛሬ ዝምታን መምረጥ፣ ነገ ለሚመጣው የከፋ ሱስ ፈቃድ እንደመስጠት ይቆጠራል።
እየመጣ ያለዉ ትዉልድ የሚፈልገው ነፃነትን ብቻ ሳይሆን፣ ያንን ነፃነት የሚገራ ጠንካራ መሪ ወላጅ ጭምር ነው። በሩን ክፍት ብንተውላቸውም አቅጣጫውን ማሳየት ግን የኛ ድርሻ ነው። ይህ ትውልድ ካለፉት ትውልዶች በበለጠ ፈጣን ነው። ነገር ግን ይህ ፍጥነት ያለ መሪ ከሆነ አደጋው የከፋ ይሆናል። በዚህ ትዉልድ ዉስጥ ያለውን ትልቅ አቅም በሱሶች እና በማንነት ቀውስ እንዳናጣው ሁላችንም ሀላፊነት አለብን።
ዶ/ር ኃይለልዑል መኮንን