03/01/2020
ልዑል ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ ኅዳር 15 ቀን 1885 ዓ/ም ተወለዱ።አባታቸው ደጃዝማች ኃይለሥላሴ ዓባይነህ ነበሩ።እናታቸው ወይዘሮ መዝለቂያ የራስ መኰንን እህት የወይዘሮ እኅተ ማርያም ልጅ ስለነበሩ የአጼ ኃይለ ሥላሴ አብሮ አደግና የቅርብ ዘመድም ነበሩ።በሰገሌ ጦርነት ላይ ከሐረርጌ የጦር አበጋዞች አንዱ ሆነው ውጊያው ላይ ተሳትፈዋል።ከጠላት ወረራ በፊት የወሎ ቀጥሎም የሐረር እንደራሴ ሆነው አገልግለዋል።በጠላት ወረራ ጊዜ በሽሬ ግንባር የጦር አዛዥ ሆነው በጀግንነት ጠላትን ተከላክለዋል።በሰሜን ግንባር ጦሩ ሲፈታ ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ በመዞር ለአንድ ዓመት ያህል በአርበኝነት ቆዩ።ጎጀብ ላይ ከተማረኩ በኃላ ወደ ኢጣልያ ተወስደው እስከ 1935 ዓ/ም ድረስ በእስረኛነት ቆይተዋል።ወደ ሀገር ከተመለሱ በኃላ የሰሜንና የበጌምድር ጠቅላይ ገዢ ሆነው ለአጭር ጊዜ ከቆዩ በኋላ በተከታታይ በአሜሪካ እንዲሁም በህንድ አገር በአምባሳደርነት አገልግለዋል።ልዑል ራስ እምሩ በአስተዳዳሪነትና በጦር አዝማችነት እጅግ የተመሰገኑና የተከበሩ ነበሩ።በ1972 ዓ/ም አርፈው ስርዓተ ቀብራቸው አዲስ አበባ መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ በክብር ተፈጽሟል።
ምስሉ ራስ እምሩ ከቤተሰቦቻቸው ጋር!