
21/09/2025
የማቋቋሚያ ደንብ ረቂቅ ሠነድ ላይ ውይይት ተካሄደ
አዲስ አበባ: መስከረም 10/2017 ዓ.ም (አማ/አእ/ስፔ/ሆ/ል) ፤ አማኑኤል የአእምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በአዘጋጀው የማቋቋሚያ ደንብ ረቂቅ ሠነድ ላይ ከጤና ሚ/ርና አቻ ተጠሪ ተቋማት እንዲሁም ከፍትህ ሚ/ር የህግ ባለሙያዎችና የሆስፒታሉ የአመራር አካላት በተገኙበት ቀርቦ ጥልቅ ውይይት ተደረጓል።
ረቂቅ የማቋቋሚያ ደንብ ሠነዱን ማዘጋጀበት ያስፈለገበትን ዋነኛ አላማ አስመልክቶ የሆስፒታሉ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር አቶ ኢዳኦ ፈጆ ሆስፒታሉ ከተመሠረተ 87 ዓመት ያስቆጠረ አንጋፋ የአእምሮ ህመምና የተሃድሶ ህክምና አገልግሎቶችን ሲሰጥ የቆየ እና በመስጠት ላይ የሚገኝ ሲሆን ሆስፒታሉ በተመሠረተበት ወቅት የነበረ የማቋቋሚያ ደንብ አሁን ከአለው የተገልጋይ ፍላጎት፣ ሃገራዊ የጤና ስርዓት ሪፎርምና ሆስፒታሉ ይዞት ከተነሳው ጥራቱን የጠበቀ የበሽታ መከላከል፤ ማከም እና የተሀድሶ ጤና አገልግሎትን በመስጠት በጥናትና በምርምር የታገዘ የአቅም ግንባታ ስራ በመስራት ከአዕምሮ ህመም የተነሳ የሚመጣ ጉዳት እና ሞትን የመቀነስ ተልዕኮና በኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት የሚሰጥ፤ በአዕምሮ ጤና ህክምና እንዲሁም በአእምሮ ጤና ምርምርና ስልጠና የልህቀት ማዕከል የመሆን ራዕዩን ተጨባጭ ወደ ሆነ ለውጥ የሚያመራ የማቋቋሚያ ደንብ መኖር እጅግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው ሲሉ በአፅንኦት አንስተዋል ።
በተጨማሪም ተገቢውን ተቋማዊ ስርአት በመዘርጋት ትኩረት በሚሹ የጤና ጉዳዮች ላይ ችግር ፈቺና ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ምርምሮችን ማካሄድ ፤ የተቀናጀ ፤ጥራቱን የጠበቀ ተገልጋይ ተኮር እና ተደራሽነት ያለው የድንገተኛና መደበኛ የአካልና የአዕምሮ ህክምና አገልግሎቶችን እና የማህበረሠብ አገልግሎቶችን ለህብረተሠቡ ለመስጠት ያለመ መሆኑ ነው የተገለፀው ።
ረቂቅ የማቋቋሚያ ደንብ ሠነዱ በሆስፒታሉ የህግ አገልግሎት ስራ አስፈፃሚ በአቶ ደበበ ለገሠ በኩል የቀረበ ሲሆን በተሳታፊዎች ገንቢ አስተያየትና ግብዓት ተሠጥቶበታል። በመጨረሻም በቀጣይ ረቂቅ የማቋቋሚያ ደኖብ ሠነዱ ከጤናው ሴክተር ሪፎርምና ከህክምና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት አኳያ እንዲሁም ከሆስፒታሉ ነባራዊ ሁኔታና የወደፊት አላማ ላይ ተመርኩዞ መሟላት ያለባቸው ጉዳዮችን በማካተት ረቂቅ የማቋቋሚያ ደንብ ሰነዱ ለውሳኔ ለሚመለከተው የመንግስት አካል እንደሚቀርብ ተመላክቷል።