15/12/2025
የዕምሯዊ ጤናማ ልጆች ባህሪያት!
የልጆች አዕምሯዊ እድገት የእውቀት (cognitive) ህጻናት እንዴት እንደሚያስቡ፣ እንደሚያስሱ እና ነገሮችን እንደሚረዱ፤ የማህበራዊ (social) ልጆች በአካባቢያቸው ካሉ ሰዎች ጋር መገናኘትን እንዴት እንደሚማሩ እና ስሜታዊ (emotional) ልጆች ማን እንደሆኑ እና ምን እንደሚሰማቸው እንዴት እንደሚረዱ ያጠቃልላል፡፡
የልጆችን አካላዊ ጤንነት ከመከታተል በተጨማሪ ዕምሯዊ ጤንነታቸውንም ችላ አይበሉ፡፡ የልጆች የአእምሮ ጤንነት ከልጆች አስተሳሰብ፣ ስብዕና፣ እድገት እና እንዲሁም ከልጆች የትምህርት ችሎታ ጋር ይዛመዳል፡፡
የአእምሮ ጤንነት ልጆች ራሳቸውን እና አካባቢያቸውን የሚመለከቱበት መንገድ ነው፡፡ ይህ ልጁ ውጥረትን እና ተግዳሮቶችን ለመቋቋም ካለው ችሎታ ጋር ይዛመዳል።
የአዕምሯዊ ጤናማ ልጅ ባህሪዎች የሚከተሉትን ያካትታሉ:
1. የተረጋጋ ስሜት መኖር
የአእምሮ ጤናማ ልጆች ጥሩ እና ጨዋነት የተሞላበት ባህሪ ያሳያሉ። ልጁ ሁል ጊዜ ቁጣ አያሳድርም ወይም ጠበኛ አይሆንም። እንደዚህ ዓይነት ልጆች ደስተኛ እና በቀላሉ መላመድ የሚችሉ፣ መደበኛ የመኝታ፣ የመንቃት፣ የመብላት እና ሌሎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎችን የሚያዳብሩ፣ በወላጆቻቸው ወይም ጓደኞቻቸዉ ላይ መጥፎና ያልተገባ ባህሪያትን የማያሳዩ ናቸዉ። እነዚህ ልጆች ለአዳዲስ ሁኔታዎች በቀላሉ መላመድ የሚችሉ ሲሆን ለሚያጋጥሟቸዉ አዳዲስ ነገሮች አዎንታዊ ምላሽን ይሰጣሉ።
2. ደስተኛ እና በራስ መተማመን
እንደዚህ ዓይነት ልጆች ደስተኞች ናቸው እንዲሁም በራስ የመተማመን ስሜት ይሰማቸዋል፡፡ ህይወትን በቀላሉ እየተደሰቱ ይኖራሉ፤ ከመጠን በላይ ጭንቀት የላቸውም።
3. ጥሩ የሆነ ተግባቦት መኖርና ለመቀላቀል ቀላል መሆን
እነዚህ ልጆች የቋንቋ ችሎታቸዉና የማህበራዊ ግንኙነታቸዉ (Social interaction) የዳበረ ስለሆነ ከጓደኞቻቸዉ ወይም ከሌሎች ሰዎች ጋር ለመግባባትና ለመቀላቀል አይቸገሩም፡፡
እራሳቸውን የቻሉ እና በወላጆቻቸው ላይ ጥገኛ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ስለዚህ ከማህበራዊ ግንኙነቶችን የማድረግ ዝንባሌ ይኖራቸዋል፡፡ ልጆች በቀላሉ ከሌሎች ልጆች ጋር በትምህርት ቤት እና በቤቱ ዙሪያ ካለው አካባቢ ጋር በቀላሉ ይቀላቀላሉ፡፡
4. ለመማር ቀላል መሆን
ልጆች ትምህርታቸዉን በትኩረት ለመከታተል ችግር አይኖርባቸውም፤ ስለሆነም በትምህርት ቤት ትምህርታቸዉን መከታተል ቀላል ይሆንላቸዋል፡፡ በእራስ የመተማመን አቅማቸው የዳበረ ስለሆነ ራሳቸውን ለመግለፅና የሚፈልጉትንና ያሰቡትን ለመናገር አይቸገሩም፡፡
5. በቂ እረፍት ማግኘት
እንደነዚህ ያሉ ልጆች በየቀኑ በደንብ እና በበቂ ሁኔታ መተኛት ይችላሉ፡፡ ብዙ የስክሪን ጊዜ (ቴሌቪዥ፣ ሞባይል ስልክ፣ ታብሌትን ኮምፒተር በመመልከት) ጊዜያቸዉን አያጠፉም፡፡ በተገቢው ሁኔታ ታዳጊዎች ከ10-13 ሰዓት መተኛት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ልጆች በየቀኑ ከ 9 እስከ 11 ሰዓት መተኛት አለባቸው፡፡
ልጅዎ ምን እንደሚሰማው እንዲናገር ይጋብዙ እና የሚያሳየዉን ባህሪ ይረዱ፡፡ የልጅዎን አካላዊ እድገት፣ ቁመና እና ገፅታ ያስተውሉ፤ ይከታተሉ፡፡ እርዳታ እንደሚፈልግ ከተሰማዎት ወይም ልጅዎ የሚያጋጥመውን ችግር ለመቋቋም የማይችል ከሆነ የሥነ ልቦና ባለሙያ ወይም የህፃናት ሀኪምን ማማከር መፍትሔ ሊሆን ይችላል፡፡
ዶ/ር አላምረው አለባቸው (በባህርዳር ዩንቨርስቲ የህፃናት ስፔሻሊስት ሀኪም እና ረዳት ፕሮፌሰር)