02/02/2026
የአይን መነፅር አይነቶች እና ጠቀሜታቸዉ
____
መነፅር (eye glasses) በፍሬም ውስጥ የተቀመጡ ሌንሶች ያሉት፣ የእይታ ችግርን ለማስተካከል፣ ለማሻሻል ወይም የዓይንን ጤና ከጎጂ ብርሀን እንዲሁም ከአደጋ ለመጠበቅ የሚያስችል ኦፕቲካል መሣሪያ ነው።
የመነፅር አይነቶች እና ጠቀሜታቸዉ
1. የነጠላ እይታ ማስተካከያ መነፅሮች (Single Vision Eye Glasses)
የአንድን እይታ (የርቀት ወይም የቅርበት) ችግርን ለማስተካከል የሚያገለግሉ መነፅሮች ሲሆኑ ማነኛዉም ችግር በሀኪም የተረጋገጠ እና የታዘዘለት ሰዉ ብቻ ሊጠቀማቸዉ ይገባል፡፡
2. ባይፎካል መነፅሮች (Bifocal Eye Glasses)
አብዛኛዉን ጊዜ እድሜያቸዉ ከ40 አመት በላይ የሆኑ ሰዎች የሚጠቀሟቸዉ ለርቀት እና ቅርበት የማየት ችግር ማስተካከያ የሚያገለግሉ ሲሆኑ በግልፅ የሚታይ መስመር ያላቸዉ መነፅሮች ናቸዉ፡፡
3. ፕሮግሬሲቭ መነፅሮች (Progressive Eyeglasses)
በአንድ መነፅር ላይ ለርቀት፣ ለመካከለኛ ርቀት (ኮምፒውተር) እንዲሁም ለቅርበት (ለንባብ) እይታን ለማገዝ የሚያገለግሉ መነፅሮች ሲሆኑ በግልፅ የሚታይ መለያ መስመር የላቸዉም፡፡
4. የኮምፒዉተር መነፅሮች
ከስክሪን የሚመጣ ሰማያዊ ብርሃንን ወደ አይን እንዳይገባ በመከላከል የዓይንን ጤና የሚጠብቁ እና የአይን ድካምን የሚቀንሱ መነፅሮች ናቸዉ፡፡ ረጅም ሰዓት ኮምፒውተር፣ ስልክ ወይም ዲጂታል መሳሪያ ለሚጠቀሙ ሰዎች ያገለግላሉ፡፡
5. የደህንነት መነጽሮች (Safety/protective eye glasses)
ዓይንን ከጉዳት (ከኬሚካሎች፣ ከፍንጣሪ ነገሮች ወ.ዘ.ተ) ለመጠበቅ የሚያገለግሉ መነፅሮች ሲሆኑ ለግንባታ ሰራተኞች፣ ላብራቶሪ፣ ፋብሪካ፣ ኢንዱስትሪ ሰራተኞች በዋናነት ያገለግላሉ፡፡
6. የስፖርት መነጽሮች (Sports Eye Glasses)
በስፓርት ጊዜ ዓይንን ከጉዳት ለመጠበቅ የሚያገለግሉ ጠንካራ መነፅሮች ሲሆኑ አትሌቶች፣ ኳስ ተጫዋቾች ፣ዋናተኞች የሚጠቀሙዋቸዉ ናቸዉ፡፡
7. የፀሐይ (Sunglasses) እና ፎቶክሮማቲክ መነጽሮች (Photochromic eye Glasses)
እነዚህ መነፅሮች ጎጂ (UV) ጨረርን ለመከላከል የሚረዱ መነፅሮች ሲሆኑ ሁሉም ሰዉ በተለይ ፀሀያማ አካባቢዎች የሚኖሩ እንዲጠቀሟቸዉ ይመከራል፡፡
በሀኪም ያልታዘዘ ወይም የሌላ ሰው መነፅር መጠቀም የሚያመጣዉ ጉዳት
አጣርቶ ማየት አለመቻል
የዓይን ድካም እና መዛል
ራስ ምታት፣ማቅለሽለሽ
የአንገት እና የትከሻ ህመም
የእይታ ችግሩ መባባስ
በህፃናት ላይ ደግሞ የእይታ እድገትን ያስተጓጉላል፣ አይን ሰነፍ ያደርጋል። “ሁልጊዜም በሀኪም የታዘዘ መነፅር ብቻ ይጠቀሙ!!!”
መረጃው የጤና ሚኒሰቴር ነው፡፡