05/11/2025
የጋሞ ዞን ጤና መምሪያ በበጀት ዓመቱ በመጀመሪያ ሩብ ዓመት ያከናወናቸውን ተግባራት ከባለድርሻ አካለት ጋር በመሆን መገምገሙ ተነገረ፤
አርባምንጭ፡ ጥቅምት 26/2018 ዓ.ም ( የጋሞ ዞን ጤና መምሪያ):
የጋሞ ዞን ጤና መምሪያ በበጀት ዓመቱ በሶስት ወራት ውስጥ በጤናው ዘርፍ የተከናወኑ አበይት ተግባራትን የዞኑ ጤና መምሪያ የማናጅመንት አባላት፣ አጠቃላይ የመምሪያው ሠራተኞች እና የአጋር ድርጅቶች ተወካዮች በተገኙበት በጥልቀት መገምገሙ ታወቋል፡፡
በዞኑ በለፉት ሶስት ወራት ውስጥ 10,569 እናቶች በሠለጠነ ባለሙያ የወሊድ አገልግሎት አግኝተዋል፣ አድሜያቸው በመውለድ ክልል ውስጥ ለሚገኙ 46,250 ሴቶች የቤቴሰብ ዕቅድ አገልግሎት አንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል፣ 15,752 ነፍሰጡር እናቶች የመጀመሪያ ዙር የቅድመ ወሊድ ምርመራ ማግኘታቸው ታወቋል፣ በሌላ በኩል እድሜያቸው ከ አንድ አመት በታች የሆኑ 12,102 ህጻናት ሁሉንም አይነት ክትባት ወስደው እንዲጨርሱ ተደርጓል፡፡
በዞኑ 134 ቀበሌያት ሜዳላይ ከመጸዳዳት ነጻ መሆናቸው በሪፖርቱ ተጠቁሟል፤ 404 የሚሆኑ የህብረተሠብ ክፍሎች ላይ የሳንባ በሽታ የተገኘባቸውና ተገቢውን ህክምና በመከታተል ላይ መሆናቸው ተጠቁሟል፤ የወባ በሽታን ከመከላከል ረገድ በተመረጡ 4 ወረዳዎች የቤት ለቤት የኬሚካል ርጭት በማካሄድ 149,490 ሰዎችን ከበሽታው መጠበቅ ተችሏል፡፡ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ከመከላከል አንጻር 48,988 የህብረተሠብ ክፍሎች ለደም ግፊት አንዲሁም 3,900 ለስኳር በሸታ የልዬ ስራ የተሠራ ሲሆን 2,301 ሴቶች የማህጸን በር ካንሰር የምርመራ አገልግሎት ማግኘታቸውን የቀረበው የበሽታ መከላከልና ጤና ማበልጸግ ዳይሬክቶሬት ሪፖርት ጠቁሟል፡፡
በዞኑ በሶስት ወራት ውስጥ በአጠቃላይ 574,650 የማህበረሰብ ክፍሎች የተመላላሽ ህክምና አገልግሎት ያገኙ ሲሆን 4,995 ሰዎች የተኝቶ ህክምና አገልግሎት አግኝተዋል፡፡ በተመሣሣይ መልኩ 5,665 የማህበረሠብ ክፍሎች የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ማግኘታቸውን የህክምና አገልግሎቶች ዳይሬክቶሬት ሪፖርት ጠቁሟል፡፡
በሶስት ወራት ውስጥ 14,281 የሚሆኑ የማህበረሠብ ክፍሎችን ለኤች.አይ.ቪ ኤድስ ምርመራ እንዲያደርጉ ማድረግ የተቻለ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 40 የሚሆኑ ሰዎች ላይ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን ለነዚህ ግለሰቦች አስፈላጊው ህክምና በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል 253 ቫይረሱ በደማቸው ለሚገኝባቸው የማህበረሠብ ክፍሎች እና 1215 ለሚሆኑ ወላጅ አጥና ተጋለጭ ህጻናት ልዩ ልዩ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል፡፡ በ 3 ወራት ውስጥ ለ 2 መድሃኒት መደብር እና መካከላኛ ክልኒክ ፈቃድ መሰጠቱን በሪፖርት ቀርቧል፡፡ በዞኑ ባሣለፍነው ሶስት ወራት ውስጥ ለ 38 የተለያዩ ባለሙያዎች ቅጥር በመፈጸም ወደ ወረዳዎች ምደባ ተሰጥቷል፡፡
በአጠቃላይ በዞኑ ለሚገኙ ወረዳዎች የፕሮግራሞችን አፈጻጸም ለመከታተል ዘርፈ ብዙ የሆነ ድጋፋዊ ክትትል ስራዎች መካሄዳቸው ታውቋል፡፡ በዞኑ የኤልክትሮኒክስ የመረጃ ስርአት በተጀመረባቸው 9 ወረዳዎች 151,574 ቤቴሠብ እና 673,906 የቤቱስብ አባላት መመዝገባቸው ታውቋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ 9,178 በጤና ተቋማት የወለዱ እናቶች የወሊድ ሰርተፊኬት ከወሳኝ ኩነት እንዲያገኙ የተደረገ መሆኑን የልማት ዕቅድና ኢኮኖሚ አስተዳዳር ሪፖርት የጠቆመ ሲሆን በአጠቃላይ በጥንካሬ የተገመገሙ ጉዳይች ይቀጥሉ ዘንድ እንዲሁም እንደ ክፍተት የታዩ ጉዳዮች ለቀጣይ ጊዚያት የድርጊት መርሃ ግብር በማወጣት ሁሉም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለፕሮግራሞቹ ስኬት ርብርብ እንዲያደረጉ አቅጣጫ ተቀምጧል።