
24/04/2025
ሆስፒታሉ ከወረቀት ንክኪ ነፃ የሆነ የህክምና ካርድ አገልግሎት በይፋ አስጀመረ
ደብረብርሃን፤ሚያዚያ15/2017 ዓ.ም ፡-
የደብረብርሃን ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከወረቀት ንክኪ ነፃ የሆነ የህክምና ካርድ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታውቋል፡፡
አገልግሎቱን የደብረብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባ የተከበሩ በድሉ ውብሸት ያስጀመሩት ሲሆን በመርሀ ግብሩ ላይ የክልል፣የከተማ፣የህብረተሰብ ተወካዮች፣የሆስፒታሉ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተግኝተዋል።
የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጥላሁን ሙሉጌታ እንደገለጹት ሆስፒታላቸው ከወረቀት ንክኪ ነፃ የሆነ የህክምና ካርድ አገልግሎት ለመስጠት ሰፊ ቅድመ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቶ ዛሬ በአውቶሜሽን ሙሉ በሙሉ ስራ ማስጀመሩን አንስተዋል፡፡
ስራው በቴክኖሎጂ መደገፉ ለታካሚዎች፣፣ለባለሙያዎችና ለሆስፒታሉ ጥቅሙ ከፍያለ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ረጂም የካርድ ሰልፍ የሚያስቀር፣የታካሚዎችን የቆይታ ጊዜ የሚያሳጥርና የካርድ ጠፋብኝ ቅሬታን የሚያስቀር እንዲሁም የተገልጋዮችን እርካታ የሚጨምር መሆኑን ለአብነት አብራርተዋል፡፡
ሲስተሙ ተቋማቸው በየዓመቱ ለህትመት የሚያወጣውን ወጪ ከመቀነሱም በላይ ተወዳዳሪ የጤና ተቋም ለመፍጠር እንደሚያስችለውም ጠቁመዋል፡
ሆስፒታሉ በ2016 ዓ.ም ብቻ ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ ለህትመት ማውጣቱን ጠቁመዋል።
ወደ ስራ የገባው አዲሱ ቴክኖሎጂ ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሆነበት መሆኑን ጠቅሰው በጤና ሚንስቴር፣በክልሉ ጤና ቢሮ፣በዶክተር ድረሴ እና በሆስፒታሉ መሸፈኑን አስታውቀዋል።
የደብረብርሃን ከተማ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ በቀለ ገብሬ በበኩላቸው እንደገለጹት ሆስፒታሉ ከወረቀት ንክኪ ሙሉ በሙሉ ነፃ የሆነ የህክምና አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ለደብረብርሃን፣ለሰሜን ሸዋ ዞንና እና ለአጎራባች ክልል ህዝብ ትልቅ ብስራትና ጠቀሜታውም ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል።
ቴክኖሎጂው ካርድ ለማውጣት የሚወስደውን ጊዜ በመቀነስ፣እንግልትን በማስቀረት፣የሠራተኛውን የስራ ጫና በማቅለል ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ፋይዳው ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ከወረቀት ንክኪ የህክምና አገልግሎት በደብረብርሃን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል መጀመሩ ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።
በከተማው በሚገኙ በሁሉም ጤና ተቋማት ለመተግበር እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የደብረብርሃን ከተማ ስማርት ሲቲ ዕቅድ ይኽ ዓይነት የዲጂታላይዜሽን ትግበራ ስራውን እንደሚያፋጥነው አመልክተዋል።
ስራው እንዲሳካ በማስተባበር ተቋማቸውና በየደረጃው የሚመለከታቸው አካላት ላበረከቱት አስተዋጽኦ፣እንዲሁም የሙያና የግብዓት ድጋፍ ያደረጉ ተቋማትንና ግለሰቦች አመስግነዋል።
የደብረብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባና የሆስፒታሉ የቦርድ ሰብሳቢ የተከበሩ በድሉ ውብሸት እንደተናገሩት ዲጂታላይዜሽን አገልግሎት አሰጣጥ በማቀላጠፍ የመልካም አስተዳደር ችግር መፍቻ አንዱ መሳሪያ መሆኑን አንስተዋል።
ዘመኑ የሚጠይቀውን በቴክኖሎጂ ተደግፎ ፈጣንና ቀልጣፋ የህክምና አገልግሎት ለህብረተሰቡ መስጠት መቻል ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።
ጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች ወደ ዲጂታል ቴክኖሎጂ መግባታቸው ተገቢና አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው ስራው ወደፊትም ውጤታማ ሆኖ እንዲዘልቅ ሁሉም የየድርሻውን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ ከንቲባ በድሉ አሳስበዋል።
ስራው በውጤታማነት እንዲጠናቀቅ ያደረጉ አካላትን ሁሉ አመስግነዋል።
Debre Birhan Comprehensive Specialized Hospital
Debre Birhan Comprehensive Specialized Hospital Laboratory