24/07/2023
የአእምሮ መስፋፋት (neuroplasticity)
*********************************
የሰው ልጅ የላእላይ አዕምሮ ክፍል ያለውን አካላዊ አደረጃጀቶችን ከተግባሩ አንጻር ስንመለከተው በግርድፉ ለሶስት ከፍለን ማየት እንችላለን። እኒህም 1) የመረጃ መቀበያ (sensory area) 2. የመረጃ መገምገሚያ እና ውሳኔን ማምረቻ (association are) 3. አስፈጻሚ (motor area) ናቸው። ቀለል ባለ መልኩ መልኩ አምስቱ የስሜት ህዋሳት መረጃ ተቀባይ፡ ውሳኔ ሰጭ፡ እና አስፈጻሚ ማለትም እንችላልን። ይህ የላእላይ የአዕምሮ አካባቢ ጤናው እጅግ ወሳኝ ነው። ለምሳሌ መረጃ መቀበያ sensory area ካልሰራ እሳት እየነደደብህ አያምህም። ውሳኔ አስፈጻሚ motor area ያልነው ቢታመም እሳት ቢያቃጥልህም እጅህን ማዘዝና ማንሳት አትችልም። association area ካልሰራማ ጭራሽ ማሰቢያ የለህም እንደማለት ነው።
እነዚህ ጣቢያዎች ታዲያ ከቀሪ የሰውነት አካላችን ጋር በነርቭ መስመር የተያይዙ ናቸው (Somatotopy) ። የላእላይ አዕምሮ ክፍል በ ነርቭ ክር ከሙሉ ሰውነት ጋር ታያይዟል። በሌላ ቋንቋ እግራችን ታች ላይ ቢንቀሳቀስም የላእላይ አዕምሮ ክፍል ላይ የ እግር መቆጣጠርያ ጣቢያ አለው ማለት ነው። የ ጣቢያው ስፋት ግን በ አካሉ ግዝፈት አይወሰንም። ምሳሌ ታፋችን ሰፊ ስለሆነ አዕምሮ ውስጥ ሰፊ መቆጣጠርያ ጣቢያ አለው ማለት አይደለም። ይልቅ እንደ አካሉ ስራ ምጥቀት የላእላይ አዕምሮ ላይ ያለው መቆጣጠርያም ይሰፋል። ለምሳሌ የአውራጣት እና ከንፈር መቆጣጠርያ ጣቢያ ከወገብ ይበልጣል ። ያማለት አእምሮ ቦታውን እንደ ፓርላማ በቀሪው አካል ይዘት ልክ ድርሻ ቦታ አይሰጥም ማለት ነው፡፡
ይህንን ለመጻፍ ያስነሳኝን ቁምነገርን ላውጋ። የሰው ልጅ አዕምሮ የማይለወጥ ድንጋይ አይደለም። እንደ አዋዋላችን ይዘቱ ይሰፋል ወይም ይጠባል (neuroplasticity)። እንዲያውም ከልብ ካየነው አዕምሮ የነጋዴ ባህሪ አለው። ለምሳሌ አንድ ባለ ሆቴል አብዛኛው ደንበኞቹ ቡና የሚጠጡ ከሆነ ቡና የሚሸጥበትን ቦታ የሰፋ የለማ የተደራጀ ያደርገዋል። ልክ እንደነጋዴው አእምሮ የሚደርሰውን መረጃ አይነት ተመርኩዞ የአዕምሮን መረብን አካላዊ ይዘቱን ያሰፋዋል። ሲብራራ የ አርሰናል ተጨዋቾች አእምሮ ውስጥ ያለው የእግር መቆጣጠርያው የአእምሮ መረብ ወይም ታይፒስቶች ያላቸው የአዕምሮ እጅ መቆጣጠርያው የነርቭ መረብ ከሌላው ደህኔ አንጻር የበለጸገ የዳበረ እና ሰፊ ነው ማለት ነው። ይህ ማለት የአእምሮ ኔትወርክ በሚሰጠው መረጃ መሠረት ይሰፋል ይጠባል ወይም “wiring” and “rewiring” የአእምሮ ሃያት ነው:: በተቃራኒው የማያስፈልጉ የአዕምሮ መረቦች ይወገዳሉ (synaptic pruning) በቦታው አዳዲሶች ይዋቀራሉ። ኢማን ከፍም ዝቅም ይላል ልበል ይሆን።
ቁም ነገር 👉 ወደ አዕምሮ የሚገቡ ነገሮች ካልተቆጣጠርናቸው ትልቅ ጣጣ ያመጣሉ። ለምሳሌ አንድ ሰው ሁልጊዜ አልኮል የሚጠጣ ከሆነ የአልኮል የሚፈጥረው ትልቅ የሆነ ዶፓሚን ክምችት neuroplastic change አዕምሮ ላይ ያመጣል። ይህ ለውጥም የግድ ሁልጊዜ አልኮሆል ለማግኘት የሚዳክር ወይም የሚያለቅስ የአዕምሮ መረብ እንዲዘረጋብን ያደርግብናል። ባጭሩ አዕምሯችን ላይ ጠጅ ቤት ተከፍቶ ጠጭ ኒውሮኖች እየጠበቁ ነው ማለት ነው። በተመሳሳይም ጫት ቃሚም አእምሮው ላይ ጫት ቤት አለ ቢባልም ትክክል ነው። ጫት የጫኑ መኪኖች እስከሚደርሱ ሲያፋሽጉ ያየኋቸው ሰዎችን የሚመስል የ አእምሮ ሰፈር ሰውነታችን ውስጥ ተፈጥሯል ማለት ነው...
ከ Prof. KH Abate የተወሰደ