
02/04/2024
በጋምቤላ ክልል አልፎ አልፎ የሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አስገነዘቡ።
ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ እና ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ቴንኩዌይ ጆክ በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል።
ከጋምቤላ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት (መጋቢት 24/ 2016 ዓ.ም)
ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በክልሉ አልፎ አልፎ የሚከሰተውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የተፎካካሪ ፓርቲዎች ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።
ሰሞኑን የተከሰተን የጸጥታ ችግር በመፍታት ሰላሙን ወደ ቀድሞ ለመመለስ በሚደረግ ጥረት በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ አስታውቀዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ቴንኩዌይ ጆክ በበኩላቸው ሰላም በሌለበት የፖለቲካም ሆነ የልማት ስራዎችን ለማከናወን እንደማይቻል ገልጸዋል።
ስለሆነም ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት መረጋገጥ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በክልሉ ሰፍኖ የቆየውን ሰላም ለማደፍረስ የሚጥሩትን ለማጋለጥና ድርጊታቸውን ለማክሸፍ መንግስት ከሚያደርገው ጥረት በተጓዳኝ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ሊጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።
አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰጡት አስተያየት ለተፈጠረው የጸጥታ ችግር የጋራ መፍትሄ ለመሻት ከክልሉ መንግስት ጋር በቅንጅት ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አልፎ አልፎ የሚከሰተውን የጸጥታ ችግር በጋራ በመፍታት የክልሉን ሰላም ዘላቂ ማድረግ እንደሚገባ አስረድተዋል።
ተቻችሎና ተከባብሮ የመኖር የቀደመ ታሪካቸውን በማጠናከር የክልሉን ሰላም ለማስቀጠል ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ መንቀሳቀስ እንደሚኖርባቸው አመላክተዋል።
በውይይቱ ላይ ብልጽግናን ጨምሮ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ አራት የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ተሳትፈዋል።