14/06/2025
የዝንጀሮ ፈንጣጣ (mpox) በሽታ ምንድን ነው?
አዲሱ የዝንጀሮ ፈንጣጣ (mpox) በሽታ በቫይረስ አማካኝነት የሚመጣ ተላላፊ በሽታ ነው። ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1950ዎቹ በዝንጀሮዎች ላይ ነበር የተገኘው። ይህ በሽታ ዘር፣ ሃይማኖት፣ እድሜና ጾታ ሳይለይ ማንኛውንም ሰው ሊይዝ ይችላል። ደግነቱ ብዙ ሰዎች ሙሉ በሙሉ ይድናሉ፣ አንዳንዶቹ ግን በጸና ሊያምና ሊከፋባቸው ይችላል። በሽታው በተለይ ህጻናት፣ ነፍሰ ጡር እናቶችና የበሽታ መከላከል አቅማቸው የተዳከመ ሰዎች ላይ ይበረታል።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ እንዴት ይተላለፋል?
የዝንጀሮ ፈንጣጣ ተላላፊ ህመም ሲሆን በሽታው ካለበት ሰው ወይም እንስሳ በንክኪ ሊይዘን ይችላል። በበሽታው ከተያዘ ሰው የመተንፈሻ አካላት ብናኞች፣ የቆዳ ቁስል ወይም የሰውነት ፈሳሾች አማካኝነት በቅርብ ንክኪ፣ መሳሳም፣ መተቃቀፍ፣ በግብረ ሥጋ ግንኙነት እና በቆዳ ለቆዳ ንክኪ ይተላለፋል። እንዲሁም የተያዘ ሰው ተጠቅሞባቸው ከተበከሉ ልብስ፣ የቤት እቃዎችንና ሌሎች ግኡዝ ነገሮችን በመንካት ሊተላለፍ ይችላል። ነፍሰ ጡር አናቶች ቫይረሱን ወደ ጽንሱ ሊያስተላልፉ ይችላሉ።
የበሽታው ምልክቶች ምንድን ናቸው?
የበሽታው ምልክቶች መታየት የሚጀምሩት አንድ ሰው ለቫይረሱ ከተጋለጠ ከሳምንት በኋላ ሲሆን አንዳንዴ በቶሎ ወይም ሌላ ጊዜ ዘግየት ብሎ ሊጀምር ይችላሉ። የተለመዱ ምልክቶች ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ የመገጣጠሚያ ህመምና ድካም ጨምሮ የጉንፋን ዓይነት ምልክቶች ነው። ቆዳ ላይ የሚወጣ ቁስል / ሽፍታ ዋነኛው መገለጫው ነው። ይህ የቆዳ ምልክቶች መጀመሪያ ላይ ጠፍጣፋ ቀላ ያለ ሽፍታ ሆኖ ይጀምርና ከዚያ አብጦ ፈሳሽ ይቋጥራል። በመቀጠልም ይፈርጥና ይቆስላል። ይህ ቁስል በፊት ላይ፣ በአፍ ውስጥ፣ እና እንደ እጆች፣ እግር፣ ደረት፣ የመራቢያ አካላት ወይም ፊንጢጣ ያሉ ሌሎች የአካል ክፍሎች ላይ ሊወጣ ይችላል። ቁስሉ ሲቆይ ይደርቅና ተቀርፍቶ ይወድቃል። ከዚያም በአዲስ ቆዳ ይተካል።
በተጨማሪም የተለያዩ ቦታዎች ላይ የሚዎጡ ንፍፊቶች ማበጥ ያሳያል። ምልክቶቹ ብዙውን ጊዜ ከ2-4 ሳምንታት ይቆያሉ።
ከቁስሉ ላይ ናሙና በመውሰድ በላብራቶሪ ምርመራ ማድረግ ይችላል።
ህክምናው ምንድን ነው?
ህክምናው በዋናነት የተያዘውንን ሰው ኳራንቲን ማድረግ ነው። ለታማሚው ቀላል ማስታገሻዎች ይበቁታል። የትኩሳት ማብረጃ መድሃኒት መውሰድ ወይም የህመም ማስታገሻ መዋጥ በቂ ሊሆን ይችላል። ቁስሎች እስኪድኑ እና አዲስ ቆዳ እስኪወጣ ድረስ ኳራንቲን መቀጠል አለበት፣ ይህ ከ 3-4 ሳምንታት ሊወስድ ይችላል።
በሽታው የተገኘበት ሰው ሊያደርጋቸው የሚገቡ ጥንቃቄዎች
👉ከተቻለ በቤት በተለዬ ክፍል ውስጥ ኳራንቲን በማድረግ ከሌሎች ጋር የቅርብ ግንኙነት ከማድረግ መቆጠብ
👉እጅን በተደጋጋሚ በሳሙና እና በውሃ ይታጠቡ ወይም በሳኒታይዘር እጅ ማጽዳት
👉ማስክ ማድረግ
👉ከሌሎች ጋር የምንጋራቸው እቃዎች መኖር የለበትም።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ ክትባት መውሰድ ኢንፌክሽንን ለመከላከል ይረዳል። ክትባቱ በተለይም በሽታው ካለበት ሰው ጋር በተገናኘን በ4 ቀናት ውስጥ መሰጠት አለበት።
(Doctors from TGH)