
28/04/2022
ሴቶችን ለአመራርነት ለማብቃት የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ ።
ጤና ኢንስቲትዩት ፡ ሚያዝያ 19 ቀን /2014 ዓ.ም
*************
ሴቶችን ለአመራርነት ለማብቃት የሚስችል ሥልጠናም ተሰጥቷል፡፡
ሥልጠናዉን በንግግር የከፈቱት የጅማ ዩኒቨርሲቲ ጤና ኢንስቲትዩት የአስተዳደር እና ልማት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ዝናሽ ሠለሞን እንዳሉት፤ ሴቶችን በማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፎች ለማብቃት የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል ።
በዋናነት የሴቶች ተሳታፊነት እና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥና ሴቶችን ለኃላፊነት ለማብቃት እየተደረገ ባለዉ ጥረት ዉስጥ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ገልጸዉ ከዚህ በተሻለ መልኩ ዉጤት ለማስመዝገብ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎችን መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አክለዉም፤ ሴቶች ለኃላፊነት ደረጃ ራሳቸዉን ለማብቃት ጥረት በማድረግ ለዉጤታማነት መትጋት እንዳለባቸዉ ጠቅሰዉ በየጊዜዉ ሴቶችን ለማብቃት የሚሰጡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎችን ወደ ተግባር በመቀየር ሊቀዉ መገኘት እንዳለባቸዉም አሳስበዋል።
የሴቶችን የአመራርነት አቅም ማጎልበቻ ዙሪያ የጥናታዊ ጽሁፍ በማቅረብ ሥልጠና የሰጡት አቶ ታደለ ማሞ ናቸዉ፡፡
አቶ ታደለ ማሞ ሥልጠናዉን በሰጡበት ወቅት እንዳሉት፤ ሴቶችን ማብቃት እና ደህንነታቸውን ለማስጠብቅ ሁሉም አካል የግልና የጋራ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ሴቶችን ከማብቃት አኳያ በርካታ ተግዳሮቶች እንደሚያጋጥሙ ጠቅሰዉ ችግሮቹን ለመከላከልና ለመቀነስ እንዲሁም ያላቸውን እምቅ ችሎታ እንዲያወጡና አስተዋጽኦቸውን ማበርከት እንዲችሉ ለማብቃት ጥረት ማድረግ ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።
ለአብነትም ያደጉ ሀገራት በቅድሚያ በሴቶች እና በህጻናት ላይ ዉጤት ለማስመዝገብ እንደሚሰሩ ጠቅሰዉ በማህበረሰባችን ዘንድ ለሴቶች የሚሰጠዉን ዝቅተኛ አመለካከት በመቅረፍ በማንኛውም የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ውስጥ የመሳተፍ እድላቸዉን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል፡፡
በቀጥይም የሴቶችን የአመራር ሰጭነት ሚና ለማሳደግ በአቅም ግንባታ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም አቶ ታደለ ማሞ አስረድተዋል፡፡
በሥልጠናዉ ላይ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጤና ኢንስቲትዩት የተዉጣጡ ሴት ሰራተኞች ተሳትፈዋል፡፡Telegram:- https://t.me/juihealth