
19/07/2025
የልብ ደራሾቹ ጥንዶች
ክፍል አንድ
ዶክተር ኦብስኔት መርዕድ የዛሬ 13 ዓመታት ገደማ የህክምና ተማሪ እያለች ከአሜሪካን ተነስታ ወደኢትዮጵያ የመጣችው ለከፍተኛ ትምህርቷ የምርምር ሥራዎችን ለማከናወን ነበር። በወቅቱም ለምርምር ሥራዋ ምርጫዋ የነበረው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ነው።
በሆስፒታሉ ያገኘችው የልብ ሃኪም የሆነው ዶክተር ስንታየሁ ወደኢመርጀንሲ ክፍል ወስዶ ከህክምና ትምህርት ቤት ተመርቆ በክፍሉ ተመድቦ ይሠራ ከነበረው የልብ ሃኪሙ ዶ/ር ተስፋዬ ጋር የምርምር ሥራዋን እንድታከናውን ያገናኛታል። ይሄ አጋጣሚ ነበር ዶ/ር ኦብስኔት መርዕድ እና ዶ/ር ተስፋዬ ተሊላን ያገናኛቸው። ባለሙያዎቹ እየተግባቡ፣ እየተላመዱም ቀጠሉ።
በሂደት ዶክተር ተስፋዬም ወደ አሜሪካ ተጓዘ። ለከፍተኛ ትምህርቱ ፈተናውን አልፎ የገባበት የህክምና ትምህርት ቤት ከዶ/ር ኦብሲኔት ጋር በቅርበት እንዲገናኙ አስቻላቸው። የከፍተኛ ትምህርታቸውንም አንድ ላይ ተማሩ። ሕይወት በአጋጣሚ ያገናኛቸው ሁለቱ ሃኪሞች በሙያ ከመተባበርም አልፈው በጋብቻ ተጣመሩ። ጥንዶቹ የአራት ልጆች አባትና እናት ለመሆንም በቁ።
አዳማ ተወልዶ ያደገው ዶክተር ተስፋዬ ተሊላ እንደሚናገረው፤ የህክምና ትምህርትን የተማረው ተወልዶ ባደገበት ኢትዮጵያ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ህክምና ኮሌጅ ውስጥ ነው። ‹‹ከህክምና ኮሌጁ ትምህርቴን ያጠናቀቅኩት እአአ በ2008 ነው። ትምህርቴን እንደጨረስኩ ለአንድ ዓመት ከ10 ወራት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ኢመርጀንሲ ክፍል ተቀጥሬ ሳገለግል ቆይቻለሁ›› ይላል።
የልብ ህክምና መማር ፍላጎት እንደነበረው የሚያስታውሰው ዶክተር ተስፋዬ፤ በዛን ጊዜ የልብ ህክምና ትምህርት በሀገር ውስጥ ባለመኖሩ በአሜሪካ ተምሮ ተመልሶ በሀገሩ ለመሥራት አቅዶ ቢጓዙም ከዶክተር ኦብስኔት ጋር የጀመሩት ግንኙነት ግን በአሜሪካ እንዲቆይ እንዳስገደደው ይናገራል። ለስምንት ዓመት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ህክምና ኮሌጅ የተማረውን ትምህርት በማሳደግ በተጓዘበት ሀገረ አሜሪካ ለሰባት ዓመታት ያህል ተምሮ በልብ ህክምና ስፔሻላይዝድ ማድረግ መቻሉንም ነው የሚገልጸው።
ለስምንት ዓመታት በአትላንታ በሚገኝ ህክምና ተቋም በልብ ሃኪምነት እየሠራ የሚገኘው ትውልደ ኢትዮጵያዊው ሃኪም ዶክተር ተስፋዬ፤ ከዶክተር ኦብስኔት ጋር በጋብቻ ተጣምረን አራት ልጆች ወልደን እያሳለፍነው የምንገኘው በትዳርም በሙያችንም ስኬታማ የሆነ ኑሮ መሆኑንም ይናገራል። ‹‹ነገር ግን ስኬት ሲደረስባት ቶሎ ታረጃለች›› የሚለው ዶክተር ተስፋዬ፤ ስኬት ምንድነው ? የሚለው ጥያቄ ከባለቤቱ ዶክተር ኦብስኔት ጋር ሁሌም የሚያሰላስለው ሃሳብ መሆኑንም ይናገራል።
ዶክተር ኦብስኔት ከፍተኛ ህክምና ባለመኖሩ በህጻንነት እድሜዋ እህቷን አጥታለች፣ ዶክተር ተስፋዪ ደግሞ በቅርቡ አጎቱ በልብ ጉዳይ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። አጎቱ የሞተ ቀን እሱ በአሜሪካ የ 92 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ ሴትዮ አክሞ አድኗል። ስለዚህ ‹‹እንዴትስ ተሳካልን እንላለን? ያሳደገን ሕዝብ መዳን በሚቻል ህመም እየረገፈ ተሳክቷል ማለት አይቻልም›› ሲል ይቆጫል።
ዶክተር ኦብስኔት አሜሪካን ሀገር ከፍላ ነው የተማረችው። ዶክተር ተስፋዬ ግን በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ህክምና ኮሌጅ ቁርስ፣ ምሳና እራት እየተመገበ ስምንት ዓመት የተማረው በነጻ ነው። በመሆኑም አገልግሎት መስጠት ውዴታ ሳይሆን ግዴታ መሆኑን ያስረዳል።
“አብልቶ፣ አጠጥቶ፣ አስተምሮ ለዚህ ክብር ያበቃኝን ጥቁር አንበሳ ሆስፒታልና ሕዝቤን በተራዬ ማገልገል አለብኝ›› ብሎ በበጎ ተግባር ላይ መሠማራቱንም ይናገራል። የኸርት አታክ ኢትዮጵያ ፋውንዴሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ኦብስኔት መርድ ፋውንዴሽኑ የተመሠረተው በአሜሪካ ሀገር ይሁን እንጂ በኢትዮጵያም የተመዘገበ ድርጅት ነው ትላለች።
ኸርት አታክ ኢትዮጵያ (Heart attack Ethiopia) የበጎ አድራጎት ድርጀት አቅም ላጡ የልብ ሕሙማን እያገዘ ይገኛል። ኑሯቸውን በአሜሪካ ያደረጉት እነዚህ ጥንዶች ከተለያዩ በጎ አድራጊዎች ባሰባሰቡት ገንዘብ ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ 33 የሕክምና ባለሙያዎችን አስተባብረው ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት ለአራተኛ ጊዜ በሶስት ማዕከላት የልብ ቀዶ ህክምና እየሰጡ ናቸው።
ዶክተር ተስፋዬ እንደሚገልፀው ብዙ ላይሆን ቢችልም የአንድ ሰው ሕይወት ማገዝም አስፈላጊ ነው። የበጎ አድራጎቱ መሠረቱም ይሄ ነው። ገንዘብ ተርፏቸው ወይም ዝነኛ ለመሆን አሊያም ሌላ ምክንያት አንግበው አይደለም ወደ ኢትዮጵያ የመጡት። እንደእርሱ ማብራሪያ፤ በመጀመሪያ ተግባሩ በትንሹ ይጀመር በሚል ሃሳብ ስድስት ባለሙያዎችን ይዘው መጥተው ለ32 ሰዎች ነበር የሠሩት። ሆኖም የነገሩ አስፈላጊነት ሥራውን እንዲያድግ አደረገ። ትግበራው ግን በቋፍ የቆመ ነገር እንደነበር ለመገንዘብ አስችሏል።
ይሄ ሁሉ አገልግሎት ፈላጊ እያለ ቢያድግ ጥሩ ነው የሚል ግፊት ነበር፣ እነሱም የበለጠ ለመሥራት ተነሳሱ። አክመውና ፈውስ ሰጥተው በሚሄዱት ሳይሆን አገልግሎቱን ባላገኙት ያዝናሉ። ለዚህም ነው ወደ ኢትዮጵያ መመላለስ ያዘወተሩት። 33 ባለሙያዎች ይዘው በመምጣት ከ32 ታካሚ በመነሳት በዚህ ዙር እስካለፈው ረቡዕ ማለዳ ድረስ 135ኛ ታካሚዎችን ልብ ፈውሰዋል።
ይህንን ዙር ሲያጠናቅቁ 150 ሰው ቀዶ ህክምና ሊሰራለት ይችላል ብለው ያስባሉ። ትልቅ ችግር መሆኑን ተገንዝበዋል። በመሆኑም ቆርጠው ተነስተዋል። ነገር ግን ብቻቸውን የሚጨርሱት እንዳልሆነ ያምናሉ። የህክምናው ወጪና ድጋፍ የኸርት አታክ ኢትዮጵያ ፋውንዴሽን ሥራው ሲጀመር በሁለታቸው አቅም ነበር። ይሄንን ያህል ታካሚ ለማከም እንችላለን በሚል አልነበረም የጀመሩት። ነገር ግን በአሜሪካ መኖራቸው ለትግበራው ጥቅም ማስገኘቱን የፋውንዴሽኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ኦብስኔት ሀብት በማሰባሰብ ህክምና የሚያስፈልጋቸውን ኢትዮጵያውያንን መደገፍ አለብን በሚል በመጀመራቸው ብዙ ጊዜ አስፈላጊ ቁሳቁሶችንና መድሃኒቶችን በርዳታ እያገኙ መሆኑንም ትናገራለች።
ዶክተር ኦብስኔት እንደምትናገረው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ መተዳደሪያ ሥራቸውን አቁመው ነው። ነገር ግን ብዙ ወጪዎች የሚሸፈኑት አሜሪካ በሚገኙ የተለያዩ ኩባንያዎች ነው። ግለሰቦችም ድጋፍ ያደርጋሉ። አሁን የገንዘብ ማሰባሰብ እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛሉ። በመጀመሪያ ዙር ሲመጡ ይዘው የመጡት 350 ሺህ ዶላር የሚፈጅ ቁሳቁስ ነበር።
አገልግሎቱን የሰጡት በአንድ ቦታ በልብ ማዕከል ብቻ ነበር። አሁን አገልግሎት መስጫ ቦታን ወደ ሶስት ቦታ አሳድገዋል። በጥቁር አንበሳ ስፔሻይዝድ ሆስፒታል፣ በልብ ህሙማን ማዕከል እና በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል እየሠሩ ይገኛሉ። መስፋፋታቸው ደግሞ አስፈላጊ ቁሳቁሶች እንዲጨምር ያደርጋል የሚሉት ዶክተር ኦብስኔት፤ በዚህ የልብ ደራሾቹ ጥንዶች ዙር ይዘው የመጡት ቁሳቁስ ሁለት ሚሊዮን ዶላር ዋጋ የሚያወጣ ነው። ብዙ ርዳታ ያገኙትም ሥራቸው ከታየ በኋላ ነው።
እንደ ዶክተር ተስፋዬ ገለፃ በዚህ ጉዳይ ብዙ ገንዘብ ያወጣሉ፤ ይሁን እንጂ በተግባሩ ደስታቸው እጥፍ ድርብ ሆኗል። ለተግባሩ ኩባንያዎች እገዛቸው ትልቅ እየሆነ ነው። ሥራውን ውድ የሚያደርገው የሚሠሩበት እቃ ዋጋው ውድ በመሆኑ ነው።
ባለሙያዎችንም ማጓጓዝ በራሱ በጣም ውድ ነው። እንደገና ደግሞ 125 የሚደርሱ ሻንጣዎችን ይዘው ነው የመጡት። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከመጀመያው ዙር ጀምሮ ተግባሩን ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በሚኖራቸው ጉዞ ወቅት እያገዘ ይገኛል። የነጻ ትኬት እና የቅናሽ ትኬት ተጠቃሚ አድርገዋቸዋል። የሚጓጓዙ ጭነቶችም በነጻ እንዲጓጓዝ በማድረግ ለትግበራው ስኬት ተባባሪ ሆኗል።
የጤና ሚኒስቴር የችግሩን ግዝፈት በመገንዘብ ሥራው እንዲሳለጥና ታካሚዎች አገልግሎቱን እንዲያገኙ በማድረግ በኩልም እገዛ አድርጓል። ችግሩ ብዙ ቤተሰብ ላይ ተጽእኖ በማሳረፍ እየጎዳ መሆኑ ታውቋል። በመጀመሪያ ዙር የመጡ ጊዜ የልብ ጉዳይ ያን ያህል ችግር ነወይ የሚሉ ነገሮች ይነሱ ነበር። አሁን በሚታይ ሁኔታ ሆኗል።
በህክምናው ሰዎች ታክመው እየዳኑ ናቸው። የዳኑት ራሳቸው ምስክርነት እየሰጡ ይገኛሉ። አሁን የቀረበው አገልግሎት በቂ ነው የምንልበት ደረጃ ላይ አይደለንም ይላሉ። ጅማሮው ጥሩ ሆኖ ተገኝቷል። አገልግሎቱ በርዳታ ደረጃ በመሆኑ እንጂ በዋጋ ቢተመን ውድ ነው። ለማስቀጠል የሚቻልበትን ሁኔታ እየሞከሩ መሆኑን ዶክተር ተስፋዬ ያስረዳል።
በቀጣይ ሳምንት አምዳችን የኸርት አታክ ኢትዮጵያ (Heart attack Ethiopia) በአራተኛ ዙር ህክምና የተሰጣቸው ታካሚዎች ሁኔታ፣ በትግበራው የገጠማቸውን ስኬትና ተግዳሮት በተመለከተ ይዘን እንቀርባለን ።