10/24/2025
St. Paul’s Hospital Millennium Medical College:
በጅማ ከተማ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የጤናው ዘርፍ ዓመታዊ ጉባዔ ላይ ባልደረባችን ዶ/ር ሰለሞን አሊ በጤና ሙያ መስክ የላቀ የሙያ አገልግሎት በአገር አቀፍ ደረጃ ተሸላሚ ሆነዋል። የሳቸውን የስራ አበርክቶ እንዲሚከተለው ቀርቧል፦
ዶ/ር ሰለሞን አሊ የ Medical Microbiologist ተመራማሪና ባለሙያ የኮሌጁ የ ሳይንሳዊ ምርምር ጆርናል ዋና አዘጋጅ በአሁኑ ወቅት በማይክሮባዮሎጅ ትምህርት ክፍል በተባባሪ ፕሮፌሰር ማእረግና Editor-in-chief of Millennium Medical College በመሆን በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡
✅ የትምህርት ዝግጅት!
ዶ/ር ሰለሞን አሊ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በደሴ ከተማ ነው። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በጅማ ዩኒቨርሰቲ በ Medical Laboratory Science የወርቅ ሜዳሊያ አግኝተው ተመረቁ።
በመቀጠልም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በ Medical Microbiology ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። በዚህም ወቅት እጅግ ከፍተኛ ውጤት በመምጣት ነው ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት።
ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ ከጀርመን ሀገር Medical research -International Health, Ludwig-Maximillians-Universitat Muenchen አግኝተዋል። የ ፒ.ኤች.ዲ ትምህርታቸው የምርምር ትኩረት በተለይ የቲቢ በሽታ አምጭ ተህዋስያን ስርጭት በማረሚያ ቤትና በተቀረው ማህበረሰብ የመተላለፍ ሁኔታ ላይ ነው።
✅ የስራ አለም!
ዶ/ር ሰለሞን አሊ ከጅማ ዩኒቨርስቲ ከፍተኛ ውጤት በማግኘታቸው ዩኒቨርሰቲው ረዳት ሌክቸረር አድርጎ ቀጠራቸው። ከጥቂት አመት በኋላም ዩኒቨርሰቲው ሌክቸረር እና የማይክሮባዮሎጅ ዩኒት ኃለፊ አደረጋቸው። ዩኒቨርስቲውን እስከሚሰናበቱበት ጊዜ ድረስ በረዳት ፕሮፌሰርነት ነበር ያገለገሉት።
እ.ኤ.አ መስከረም 2011 የቅዱስ ጳወሎስ ሆስፒታል የማይክሮባዮሎጅ ትምህርት ክፍል በረዳት ፕሮፌሰር ደረጃ ተቀላቅልዋል። በኋላም ጥቅምት 2012 የኮሌጁ የ Medical Microbiology እና የ Medical research-International Health በሚል በተባባሪ ፕሮፌሰርነት ማእረግ እንዲሰሩ ሴኔት ወሰነላቸው።
1️⃣ የላቀ ምርምርን በተመለከተ!
ዶ/ር ሰለሞን አሊ ምርምር ለማካሄድ እና ሙያዊ ተፅእኖን ለማምጣት፤ ታዋቂ ከሆኑ የሀገር ውስጥና አለም አቀፍ የጤና ተመራማሪዎች ጋር በመተባበር በሀገራችን በመህበረሰቡ ላይ ከፍተኛ ተግዳሮት በደቀኑ ተላላፊ በሽታዎች በዋናነት በኮቪድ-19፣ ቱበርክሎሲስ (ቲቢ)፣ መድሃኒት የተለማመደ ጀርም፣ እና በሆስፒታል ውስጥ በመዘዋወር ለታካሚዎች ተጨማሪ ኢንፌክሽኖችን በሚያመጡ ጀርሞች ላይ ምርምር ሰርተው ከ 54 በላይ የምርምር ጽሁፎችን በአለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ተጽዕኖ ባላቸው፤ ለአብነት ያህል ላንሴት ግሎባል ሄልዝ፣ ኔቸር ኮሚኒከሽን በማሳተም በጤናው ዘርፍ ምርምር በሚያደርጉ የጤና ፖሊሲ ለሚቀርጹ እና ለአጠቃላይ የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ለንባብ አብቅተዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ዶ/ር ሰለሞን በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚለኒየም ሜዲካል ኮሊጅ ባለቤትነት የሚታተም “ሚሊኒየም ጆርናል ኦፍ ሄልዝ“ የጤና ምርምር መጽሄት ያቋቋሙና የዚህ መጽሔት ዋና አዘጋጅ ሆነው ከአራት አመት በላይ አገልግለዋል።
መጽሔቱ ከሳይንሳዊ የጤና ጥናትና ምርምር፣ እንዲሁም ከዕለት ተዕለት የህክምና አገልግሎት የሚፈጠሩ የጤና እውቀቶችን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ አዘጋጅቶና ሰንዶ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ለሚገኙ የጤናው ዘርፍ ተመራማሪዎችና ባለ ድርሻ አካላት በድህረ-ገጽ ላይ እያሳተመ ተደራሽ የሚያደርግ ነው።
2️⃣ ለጤና ዘርፍ የላቀ ሙያዊ አስተዋፅኦ!
ዶ/ር ሰለሞን አሊ ከሀገር ውስጥና አለም አቀፍ የጤና ተመራማሪዎች ጋር በመተባበር ባደረጉት የምርምር ገንዘብ የማግኘት ውድድር ከአለም አቀፍ የምርምር ገንዘብ ሰጭ ተቋማት በድምሩ 6,000,000 ዩሮ የሚጠጋ ገንዘብ ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሚዲካል ኮሌጅ፣ እና ሌሎች የሃገራችን ዩኒቨርስቲዎችና የምርምር ተቋማት ተጠቃሚ ኣንዲሆኑ አድርገዋል።
ከተጠቀሰው ገንዘብ ውስጥ 24% (1,500,000 ዩሮ የሚጠጋው) በእርሳቸወ ዋና ተመራማሪነት ቅዱሰ ጳውሎስን እና ጅማ ዩኒቨርስቲን ተጠቃሚ አድርግዋል።
በዚህም መሰረት ከሚያደርጉት የጤና ምርምር በተጨማሪ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ውስጥ የጤናውን አገልግሎት በተጨባጭ ያሻሻሉ ወይም የሚያሻሽሉ ቀጥሎ የተዘረዘሩ ስራዎችን ሰርተዋል።
✨1. በቅዱስ ጳውሎስ ውስጥ የመጀመሪያውን የሞለኪውላር ምርምርና አንደ ኮቪደ-19 አይነት ወረርሽኝ ወደ ፊት ቢከሰት አገልግሎት የሚሰጥ፣ ዘመኑ የሚጠይቀውን የሞለኪውላርና ፌኖታይፒክ የማይክሮ ባዮሎጂ ምርመራ ማድረግ የሚያስችሉ ዘመናዊ መሳሪያዎች የያዘ ላቦራቶሪ በ2014 አቃቁመዋል።
በአሁኑ ጊዜ ላቦራቶሪው የህጻናት መተንፈሻ አካላትን የሚያጠቁ 8 ቫይርሶችን አየመረመረና በጽኑ ህሙማን ታካሚ ክፍል ውስጥ የተኙ ታካሚዎች በሰውነታቸው ውስጥ የተሰራጩ ጀርሞችን ምርምራ ማድረግ፣ መለየትና ለጸረ-ጀርም መድሀኒት ያላቸውን ግብረመልስ የመመርመር አገልግሎት አየሰጠ ይገኛል።
✨2. በወረርሽኝ ወይም ደግሞ ቀን በቀን የህክምና አገልግሎት ጊዜ አለም አቀፍ ትኩረት የሚስቡ ህመሞች ሲያጋጥሙ ናሙናዎችን ለአጭር/ለረጅም ጊዜ ሊያቆይ የሚችል የባዮባንኪንግ ስርአት በቅዱስ ጳውሎስ ውስጥ ዘርግተዋል።
✨3. በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታልና በሀገራችን ሆስፒታሎች ውስጥ አየታየ ያለውን የጀርሞች ስርጭት በተለይ ደግሞ ጸረ-ጀርም መድሃኒት የተለማመደ ባክቴሪያን ለመቆጣጠር የሚያስችል ስራ ከአውሮፓ ህብረት (ኢዲሲቲፒ3) ከጅማ ዩኒቭርስቲ፣ ከአርሲ ዩኒቨርስቲ። እና በጀርመን ሃገር ከሚገኘው ክሊኒከም ዩኒቨርስቲ ኦፍ ሙኒክ ጋር ባሸነፉት ግራንት ጀምረዋል።
ስራው በዋናነት ትኩረት የሚያድርገው በአለም አቅፍ ደርጃ ተቀባይነት ያለውን በሆስፒታል ውስጥ የጀርሞችን ዝውውር አንዲገታ የሚያስችል ስልት በመጠቅምና፣ መድሃኒት በተለማመደ ጀርም ተጠቅተው በጠና የታመሙ ታካሚዎችን የመድሀኒቱን የደም መጠን በመለካትና ህክምናውን በታካሚው ሁኔታ በማስተካክል የጀርሞችን ስርጭት በሆስፒታል ውስጥ መግታት ነው።
✨4. ዶ/ር ሰለሞን አሊ ከክሊኒኩም ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሙኒክ እና ሂስፕ ኢንዲያ ጋር በመተባበር ከ GIZ በተገኘ ድጋፍ DHIS2 ላይ የተመሰረተ የአንቲባዮቲክ አስተዳደር መመሪያን ለመተግበር የሚያስችል ሲስተም ዘርግተዋል።
በአሁኑ ጊዜ ባለሙያዎችን ለማሰልጠን ዝግጅት አያደረጉ ሲሆን፤ ይህ ዌብ ቢዝድ ሲስተም መደበኛውን የማይክሮባዮሎጂ የላቦራቶሪ ምርምራ እና የ AMR የፍተሻ መረጃን በመጠቀም ለሐኪሙ የአንቲባዮቲክ ሕክምና ምርጫ ትክክለኛ አንዲሆን የሚያግዝ ነው።
3️⃣ በማስተማርና በማሰልጠን ረገድ!
ዶ/ር ሰለሞን የሕክምና ተማሪዎችን እና ሌሎች የጤና ባለሙያዎችን በማስተማር ላለፉት 16 ዓመታት ሰረተዋል። ይህም ቅድመ ምረቃ፣ ድህረ ምረቃ፣ ስፔሻሊቲ፣ እና የፒ.ኤች.ዲ ተማሪዎችን ማሰልጠንን እና ማማከርን ይመለከታል። እሳቸው ከፍተኛ የሰው ሃይል ስልጠናን በተመለከተ ጉልህ ስፍራ አላቸው።
በአሁኑ ወቅት በቁጥር አራት የሚደርሱ የፒ.ኤች.ዲ ተማሪዎችን የሚያማክሩ ሲሆን፤ በቁጥር 14 የሚደርሱ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ምርምር በማማከር አየሰሩ ይገኛሉ።
በተጨማሪም በተለይ በተላላፊ በሽታዎች ዙሪያና በክሊኒካል ምርምር አጫጭር ስልጠናዎችን ሰጥተዋል። ለምሳሌ Capacity building training on COVID-19 sample collection, Specimen handling, and PCR testing የሚል ስልጠና ለጳውሎስ እና ከየካ ክፍለ ከተማ ለተውጣጡ የጤና ባለሙያዎች ስልጠና ሠጥተዋል። ይህም በኮቪድ ወቅት በእጅጉ አስፈላጊው ስልጠና ነበር።
በኋላም strengthen testing of SARS-CoV-2 from different sources including wastewater and specimen handling በሚል ርእሰ ላይ ስልጠና ሠጥተዋል።
በጅማ ዩኒቭርስቲ ቆይታቸውም፤ Good clinical practice (GCP) & Good clinical Laboratory practice (GCLP) የመሳሰሉ የክሊኒካል አገልግሎትና ምርምር ስልጠናዎችን ከ WHO-TDR ጋር በመተባበር ሰጥተዋል።
ምንጭ፦ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ